ኀዳር ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል የደቡብ ወሎና የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎችና አብያተክርስቲያናት ተገቢ ጥበቃ ባለማግኘታቸው የተለያዩ ቅርሶች የተዘረፉና የጠፉ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በአመት አንድ ጊዜ በሚዘጋጀው የቅርስ ጉባኤ ላይ ገለጸ፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች 37 ቅርሶች መሰረቃቸውን ይፋ ያደረጉት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ አለበል ደሴ ፣በክልሉ ከ2001 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2006 መጨረሻ ባለው ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች 124 መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ብቸኛ የሆነው የደሴ ሙዙየም በስተደቡብ አቅጣጫ ጫካ በመሆኑና ዙሪያውም ምንም ዓይነት አጥር ስለሌለውየጥበቃ ቢሮው ተሰብሮ በውስጡ የነበሩ ሁለቱም የጦር መሣሪያዎች ከነሙሉ ጥይታቸው ከመሰረቃቸውም በላይ እስከአሁንም አለመገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቅርሶች በመስታውት ዉስጥ ተቆልፈው ስላልተያዙ ለአቧራና ለአላስፈጊ ንክኪ መጋለጣቸውም ሃላፊው ተናግረዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ተገቢውን ጥበቃ ባለማግኘታቸው በሌቦች መሰረቃቸውንና አብዛኛዎቹ አለመገኘታቸውን በውይይቱ ላይ የተወሳ ሲሆን የአንኮበር ማሪያም ቤተክርስቲያን 3 የብር መቋሚያዎችና 7 የብር ጸናፅልች፤ በአንፆኪያ ወረዳ በ03 ቀበሌ አጥቆ በዓታ ማሪያም ቤተክርስቲያን 9 የብራና መጽሃፍት፣ 3 ሌሎች የመገልገያ መጽሃፌት እና 1 የመፆር የነሃስ መስቀል ተሰርቀው እስካሁን አልተገኙም።
በሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው ይማደጋ ቅደስ ሚካኤሌ ቤተክርስቲያን ውስጥ ዘራፉዎች ገብተው 2 የቅዱስ ሚካኤል ጽላት ፣ 1 የመስቀለ እየሱስ ጽላት ፣ 3 የነሃስ የመፆር መስቀል፣ 1 መጎናፀፉያ የተዘረፉ መሆኑ ለአብነት በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ በቅርስ ዘረፋው የባለስልጣናት እጅ አለበት ሲሉ ሃሳብ ያነሱት ተወያዮች እንዴት በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሳተፉ ባለስልጣናት ቅርስ ዘረፋን ይከላከላሉ ተብሎ እንዴት ይገመታል ሲሉ ሞግተዋል፡፡
በጋይንት አካባቢ ብቻ ከ30 ያላነሱ አብያተክርስቲያናት ቅርሶች መዘረፋቸውን ጥቆማ እንደደረሰው የክልሉም ሆነ የፊደራል ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ሚኒስቴር ቢያሳዉቅም ጉዳዩ ተጣርቶ የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ የቅርስ መገኛ ተቋማት 3ሺ እንደሚደርሱ ቢገመትም ሙዙየም በማሰራት ቅርሶቻቸውን በጥንቃቄ ለእይታ እያቀረቡ ያሉት ግን 13 ብቻ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ በብሄራዊ ሙዚየም ውስጥ ይገኙ የነበሩ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚዘክሩ መጽሃፍት በተቀነባበረ መልኩ በርካሽ ዋጋ ለነጋዴዎች የተሸጡ መሆናቸው የተዘገበ ሲሆን፣ እስካሁን ለኢሳት በደረሰው መረጃ የጆብ ሎድፍ 1664፣ 1700፣ 1800፣ የጀምስ ብሩስ፣ የካርሎ ሮሲኒ፣ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ይታተሙ የነበሩ የቄሳር መንግስትና የሮማ ብርሃን የተባሉ ጋዜጦች፣ 2 ሺ ኪሎ ግራም ይመዝናሉ የተባሉ የአጼ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ዮሃንስና የአጼ ሚኒሊክ ደብዳቤዎች ተቸብችበዋል።