ኀዳር ፲፪(አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቀድሞ የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው ከሰራተኛው ጋር በተፈጠረ ውዝግብ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበሩት የኢህአዴግ አባሉ አቶ አባዲ ተካ ከተሾሙ ካለፈው አመት ጀምሮ ብርሃንና ሰላም መረጋጋት ተስኖት ከቆየ በሁዋላ በቅርቡ ደግሞ ድርጅቱ በኪሳራ ምክንያት ይሸጣል መባሉ ሰራተኛውን አስደንግጧል።
በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የሚከሰሱት አቶ ተካ “ድርጅቱ እየከሰረ መቀጠል የለበትም፣ መሸጡም አይቀርም” በማለት ለሰራተኞች ከተናገሩ በሁዋላ ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ የቆዩት ሰራተኞች በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አንድም ቀን ኪሳራ አጋጥሞት ባያውቅም፣ አቶ ተካ ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ በሚወሰዱ የተበላሹ አሰራሮች የድርጅቱ ህልውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
አቶ ተካ ለብርሃንና ሰላም 800 ሰራተኞች አያስፈልጉም በማለት እድሜያቸው ከ50 በላይ የሆኑትን ወደ 400 የሚጠጉ ሰራተኞችን ለማባረር የተዘጋጁ ሲሆን፣ ሰራተኞች እንደሚሉት ልምድ ያላቸውን በማባረር አዳዲስ የኢህአዴግ ወጣት አባላት ለመቅጠር አቅደዋል። በድርጅቱ ውስጥ ከሚሰሩት ሰራተኞች መካከል 100 ያክሉ የኢህአዴግ አባላት ናቸው።
በሰራተኞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በመቃወማቸው ላለፉት 18 አመታት የሰራተኛውን ማህበር የመሩት አቶ ተስፋየ መላኩ ከስራ እና ከደሞዝ ክፍያ ታግደዋል። ሰራተኞች እንደሚሉት ድርጅቱ ስራ እንዳጣ ተደርጎ ሪፖርት የሚደረገው በኪሳራ ስም የህወሃት ንብረት ለሆነው ሜጋ የህትመት ድርጅት ለመሸጥ በመታቀዱ ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ የድርጅቱን ስራ አስኪያጅ ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።