ጥቅምት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን ተጠናክሮ የቀጠለው የገዢው ፓርቲ አፈና መንግስት ራሱ ያስታጠቃቸውን ታጣቂዎች ትጥቅ እስከማስፈታት መድረሱን ምንጮች ገለጹ
በትግራይና በአማራ ክልሎች ባለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው አፈና ቀጥሎ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ኣም የሰላም ታጋይ እየጠባለ የሚታወቅ ወጣት ሽሻይ አዘናው በመቀሌ ከተማ በትግራይ ክልል የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ገ/ህይወት ካህሳይ እና በደህንነት ሃይሎች ከሚሰራበት የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት የትግራይ
ክልል ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ታስሮ እና ቤቱ ተበርብሮ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዷል። ሽሻይ አዘናዉ የዓረና ትግራይ መስራችና ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ በቅርቡ ደግሞ ከዓረና ወደ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ የተቀላቀለ ወጣት ነው።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ቋራ በደላ ቀበሌ አካባቢ መሳሪያ የታጠቁ አርሶአደሮች መሳሪያቸውን እየተነጠቁ ነው። ትክል ድንጋይ አካባቢም እንዲሁ በርካታ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ መደረጋቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በትግራይ ክልል በምዕራባዊያን ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ዳንሻ ከተማ የአረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዘነበ ሲሳይ ጥቅምት 25፣ 2007 ዓም ከቤታቸው ተወስደው ሲታሰሩ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ቀን በሁመራ አረና የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አማረ ተወልደ ታስረዋል። ከወራት
በፊት የታሰሩትን አብራሃ ደስታንና አያሌው በየነን ጨምሮ 7 የፓርቲው አመራሮች በእስር ላይ ናቸው። በተመሳሳይ ቀን በአማራ ክልል ምዕ/ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበ እና ሶስት የድርጅቱ አባላት ተይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል። ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ ከ10
ያላነሱ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አንዱአለም አራጌ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ ናትናኤል መኮንንና ሃብታሙ አያሌው አሁንም በእስር ላይ ናቸው።
የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል እና የሰሜን ጎንደር የዞን ሰብሰቢ አቶ አግባው ሰጠኝም እንዲሁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል። ሶስት የሰማያዊ ፓርቲ የአርባምንጭ አመራሮች አሁንም ድረስ በእስር ላይ ናቸው።
በምእራብ ጎጃም በፍኖተሰላም ከተማ የመኢአድ የወረዳው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ) ሰብሳቢ የሆነው ዘሪሁን ብሬ ረቡዕ ጥቅምት 26፣ 2007 ዓም ተይዞ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስዷል።