ጥቅምት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በኢትዮጵያ እና በአረብ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሁም መንግስት ወደ አረብ አገራት በሚላኩ ዜጎች ጉዳይ ሊፈጽመው ያሰበው ስምምነት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ግምገማ ተካሂዶ ነበር።
መንግስት ተጓዝ ሰራተኞችን በሚመለከተ ያወጣው ህግ በአረብ መንግስታት እውቅና የተነፈገው ሲሆን፣ የአረብ አገራት ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች የሙያ ክህሎት የላቸውም፣ በአገሪቱ ማሰልጠኛ ተቋማት በደንብ አይሰለጥኑም የሚል ምክንያት በማቅረብ ስምምነቱን ለመፈረም ፍላጎት አለማሳየታቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
ከኤርትራ ፤ፊልፒንስ ፤ ሱዳን እና ግብፅ የሚመጡ ሰራተኞች ከኢትዮጵያውያን በተሻለ በአረቦች እንደሚመረጡ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኳታር እና የሳውዲአረቢያ ተቃውሞ መነሻው በሙስሊም አመፀኞች ላይ ከምንወሰደው እርምጃ እና ከአባይ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የግብፅን ወዳጀነት ላለማስከፋት ካላቸው ፍላጎት አንጻር ነው ብለዋል።
የጠ/ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የዶ/ር ቴዎድሮስን አቋም ውድቅ በማድረግ የአረብ አገራት የወሰዱት እርምጃ ከግብፅ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም ብለዋል። ግብፅ ራሱን ያልቻለ ደካማ መንግስት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ መንስኤው የኛ የራሳችን የዲፕሎማሲ ጥራት ችግር ነው ሲሉ አክለዋል፡፡ በሁለቱ ባለስልጣኖች መካከል የተሰጠው ምክንያት መለያየቱን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው ከመለስ ሞት በኃላ ተዳክሟል ወይስ ተጠናክሯል በሚል ጥናት እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሶ ተበትኗል።