ጥቅምት ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እንግሊዝ አገር የሚታተሙ ጋዜጠኞች ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ በቂ ሽፋን አይሰጡም በሚል ሲተቹ ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በማንሳት እንግሊዝ በኢትዮጵያ የምትከተለውን ፖሊሲ የሚነቅፉ ዘገባዎችን እያወጡ ነው።
ዘ ቴሌግራፍ ” እርዳታችን ለተበላሹ እጆች” በሚል ርእስ ባወጣው ሃተታ፣ በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያጋለጠበትን ሪፖርት በመጥቀስ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ በእየአመቱ የምትሰጠው 329 ሚሊዮን ፓውንድ ጭቆናን ለማስፋፊያ እየዋለ ነው ብሎአል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ሴቶችን እየደፈሩ፣ ህዝቡን እያሰቃዩ ባለበት ሰአት ለመንግስት እርዳታ መስጠት እውን ተገቢ ነው? ሲል የሚጠይቀው ዘ ቴሌግራፍ፣ እንግሊዝ የምትሰጠው እርዳታ ለጸጥታ ሃይሎች በቀጥታ አይደርስም በማለት ባለስልጣኑ የሚያቀርቡት መከራከሪያ ተክክል እንዳልሆነ ጠቅሷል። ከውጭ የሚመጣው እርዳታ ትምህርትቤቶችንና የጤና ተቋማትን ለመገንባት የሚውሉ ከሆነ፣ መንግስት የራሱን ገንዘብ ጭቆናውን ለማስፋፋት ያውለዋል ያለው ዘ ቴሌግራፍ፣ የውጭ እርዳታ ካለ መንግስታት የራሳቸውን ሃብት ለፈለጉት ነገር ለማዋል እድል ይሰጣቸዋል ብሎአል።
እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ ባለፈው አመት በ32 በመቶ ቢያድግም፣ ባለስልጣናቱ ገንዘቡን ማውጣታቸውን እንጅ ለአልተፈለገ አላማ መዋሉን ለመቆጣጠር አልቻሉም ሲል የሰላ ትችት ሰንዝሯል።
ዘ ኢንዲፐንደንት ባለፉት 2 ወራት የእንግሊዝ መንግስትን የውጭ ፖሊሲ በመተቸት ተከታታይ ዘገባዎችን ሲያወጣ፣ በተለይ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህገወጥ እስር ዙሪያ የእንግሊዝ መንግስት እየተከተለ ያለውን ፖሊሲ በጽኑ ተችቷል።
የእንግሊዝ የውጭ ልማት ተራድኦ ድርጅት ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው እርዳታ በቀጥታ ወደ መንግስት በጀት እንደማይገባና ህጻናትን ለመታደግ እንደሚውል ይገልጻል።
የእንግሊዝ መንግስት ለኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ማስተማሪያ የመደበውን በጀት መሰረዙ ይታወቃል። በእንግሊዝ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ተከታታይ ተቃውሞ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትን እየሳቡ ሲሆን፣ ጋዜጦቹ ተከታታይ ዘገባዎችን ማቅረብ ከቀጠሉ የአገሪቱ መንግስት ለኢትዮጵያ በሚሰጠው እርዳታ ላይ ፖሊሲውን ለመመርምር ሊገደድ ይችላል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።