የሼክ ሙሃመድ አላሙዲን ንብረት በሆነው ኢትዮ ድሪም የአበባ እርሻ የሚሰሩ ሰራተኞች ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ተናገሩ

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-  በምዕራብ ሸዋ በሆለታ ገነት የሚገኘው የሼክ ሙሃመድ አላሙዲጅ ንብረት በሆነው ” ኢትዮ ድሪም” ድሪም የአበባ እርሻ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ላለፉት ሁለት ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው በመሆኑ እነሱና ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።

ሰራተኞች አቤቱታቸውን ለድርጅቱ ሃላፊዎች ቢያቀርቡም መልስ ማጣታቸውን ገልጸዋል። አብዛኛው ሰራተኛ 600 ብር እንደሚከፈለው የሚናገሩት ሰራተኞች፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 150 ብር የቤት ኪራይ እየከፈሉ በቀሪው ገንዘብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ ለሁለት ወራት የተቋረጠባቸውን ክፍያ ተከትሎ የቤት ከራይና የምግብ ወጪያቸውን ለመሸፈን ተስኖአቸዋል።  ድርጅቱ ቀደም ብሎ የአንድ ጣሊያናዊ ባላሀብት እንደነበርና ካለፈው አመት ጀምሮ የሼክ ሙሃመድ አላሙዲ ኩባንያ እንደገዛው ሰራተኞች አክለው ገልጸዋል።