የአለም ባንክ መሪ ለዶክተሮች ጥሪ አቀረቡ

ጥቅምት ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያ የሚገኙት የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪም በምእራብ አፍሪካ የሚታየውን የኢቦላ ወረርሽን ለመዋጋት ቢያንስ 5 ሺ ዶክተሮች የሚያስፈልጉ በመሆኑ ፣ ዶክተሮች ና የጤና ባለሙያዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃዳቸውን እንዲገልጹ ተማጽነዋል። ” በአሁኑ ሰአት ይህን ሁሉ ቁጥር ያለው የህክምና ዶክተር ከየት እንደምናገኝ ሳስብ እጨነቃለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በብዙ ቦታዎች ፍርሃት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመጣበት ሁኔታ ሃኪሞች ለሙያቸው የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ 200 ሃኪሞችን እንደምትልክ ማስታወቋ ይታወሳል። የመንግስት ውሳኔ የተለያዩ አስተያየቶችን እያስተናገደ ሲሆን፣ መንግስት ሀኪሞች በፈቃዳቸው ካልሆነ እንጅ በግዳጅ መሄድ እንደሌለባቸው የሚያሳስቡ መልእክቶች በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት እየተሰራጩ ነው።