ጥቅምት ፲፮(አስራ ሥድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የመስተዳድሩ ኃላፊዎች በፖለቲካ ስልጠና እና በግምገማ መወጠራቸው ውሳኔ በወቅቱና በአግባቡ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ነዋሪዎች አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረዋል።
በእያንዳንዱ የሴክተር መስሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙጥ ኃላፊዎች የሉም ያለው ዘጋቢያችን፣ ውሳኔዎችን የሚሰጥ በመጥፋቱ የውጪም ሆነ የውስጥ አግልገሎት ቆሟል።
ኦህዴድ በአዲስ አበባ ያሉትን ከፍተኛ የአመራር አካላት ወደ አዳማ በመጥራት ለ14 ቀናት የሚቆይ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን በመስተዳድሩ ውስጥ ወኪሎቻቸው ያሉዋቸው ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶችም በተመሳሳይ መንገድ በመጥራት የፖለቲካ ስልጠና እየሰጡ ነው።
በሌላ ዜና ደግሞ ኢህአዴግ ለመስተዳድሩ የመንግስት ሰራተኞቹ ሲሰጥ በቆየው የፖለቲካ ስልጠና ላይ ለገዥው ፓርቲ ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ የነበረና የስርአቱን ችግሮች በመናገር ሲተች የቆየ ፋንታሁን የተባለ የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ ሰራተኛ መታሰሩን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
ሰልጣኙ ‹‹ደርግንም ሆነ ምኒልክን እናውቃቸዋለን፡፡ እናንተ ስለ እነሱ መጥፎውን ከምትገልጹልን እንደ 97 እንደማትገድሉና ነጻና ፍትሃዊ ምትጫ እንደምታደርጉ ንገሩን፡፡››ሲል አስተያየት መስጠቱ የኢህአዴግን ካድሬዎች አስቆጥቶ እንደነበር ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ ስብሰባው ካለቀ በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 13/ 2007 ዓ.ም
አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ የኢህአዴግ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ደህንነቶች ግለሰቡን ይዘው ወስደውታል። የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ‹‹ግንቦት 7 ብሎ ጠረጴዛ ላይ ጽፏል፡፡›› የሚል የሀሰት ክስ እንደከፈቱበት ግለሰቡ ለጋዜጣው ገልጿል።
ፋንታሁን ችሎት ተብሎ በሚጠራው ቀጨኔ መዳህኒያለም አካባቢ በሚገኝ ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ የሚገኝ ሲሆን ማክሰኞ/ ጥቅምት 18 ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል።
በስብሰባው ወቅት ከባድ ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ሰዎች ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ስልክ እየተደወለ ” ምን ለማት ፈልገህ ነው?’ እየተባሉ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከመስተዳድሩ ዜና ሳንወጣ ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ በሚመሰል ሁኔታ በርካታ ወጣቶች በሰበብ አስባቡ እየተያዙ በመታሰር ላይ ናቸው። በአለፉት ሁለት ወራት ውስጥ አዲስ አበባ በሚገኙ እስር ቤቶች በርካታ ወጣት እስረኞች የገቡ ሲሆን፣ ለመታሰራቸው የሚቀርበው ምክንያት አስገራሚ መሆኑን
የፖሊስ ምንጮች ተናግረዋል። ብዙዎቹ ወጣቶቹ ከዚህ ቀደም በአንድ ለአምስት በተደራጁና በማህበራት አባላት ሲጠኑ የነበሩ ና በመጪው ምርጫ ላይ ረብሻ ሊያነሱ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። የመስተዳድሩን የፖሊስ አዛዥ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።