ጥቅምት ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የመንግስት ሃብትና ንብረትን ላለፉት ሶስት አመታት የህዝብን ሃብት በህገወጥ መንገድ በማባከን ሪኮርድ የሰበሩ መንግስታዊ ተቋማት እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው ለተወካዮች ምክር ቤት ያዘጋጀው ሪፖርት ያመለክታል። የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ግምገማው ለኢትዮጵያ ህዝብ መቅረብ የለበትም ብለዋል።
ባለፉት 3 አመታት ሂሳባቸውን በወቅቱ ያልዘጉ መ/ቤቶች የፋይናንስና ኮሚኒኬሽን መ/ቤቶች ፣ የግዢ ኤጀንሲ፣ የንግድና አስተዳደር መ/ቤቶች፣ የፌደራል ልዩ አቃቢ ህግ ጽ/ቤት ተብለው ሲጠቀሱ፣ ስለሂሳባቸው አቋም ለመውሰድ ያልተቻለባቸው መስሪያ ቤቶች ተብለው የተለዩት ደግሞ ጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ የወሎ ዩኒቨርስቲ፣ የፋይናንስና ኮሚኒኬሽን መ/ቤቶች፣ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫና የፈተናዎች ኤጀንሲ ናቸው።
ሂሳባቸውን ካስመረመሩ በሁዋላ ሰነድ የቀሙ መስሪያ ቤቶች ተብለው የተለዩት ደግሞ የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት፣ የኢሚግሬሽን ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያና የውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ ሲሆኑ፣ ተቀባይነት የሌለው ወይም የተበላሸ አሰራር ይከተላሉ ከተባሉት መካከል ደግሞ የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ፣ ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርስቲ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ፣ አክሱም ዩኒቨርስቲ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ መልእክተኞች፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት፣ የግብርና ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ፕሮጀክት፣ የምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ዳይሬክቶሬት ተጠቅሰዋል።
አንጻራዊ የሆነ የተሻለ የሂሳብ አያያዝ አለባቸው ከተባሉት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ፣ የወለጋ ዩኒቨርስቲ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፣ የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ጨረር መከላከያ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይገኙበታል። አባ ዱላ ገመዳ የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ገንዘቡ እንደተበላ እየታየ የመንግስት ስም ጥላሸት እየተቀባ ስለሆነ የኦዲት አሰራሩ መስተካከል አለበት ሲሉ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ወቅት የጠቅላይ ኦዲተር መስሪያ ቤትን አሰራር በህዝብ ፊት በመተቸታቸው የጄኔራል ኦዲተሩ ከሃላፊነት ተነስተው አዲስ ጄኔራል ኦዲተር እንዲሾም ተደርጓል። አዲሱ ኦዲተር ሃላፊነቱን ከተቀበሉና አቶ መለስ ዜናዊ ካለፉ በሁዋላ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት የመሳሪያ ግዢና የሎጅስቲክስ አቅርቦት ወጪዎች በጄኔራል ኦደተር እንዳይመረመር ተወስኗል።