ጥቅምት ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአካባቢው ወኪል እንደገለጸው በሸኮ መዠንገር ተወካዮችና በከፋ፣ ሸካ፣ ጋምቤላና ቤንች የዞን አመራሮች መካከል በሃይማኖት አባቶች አማካኝነት በቴፒ ውይይት እያደረጉ ነው።
የአካባቢው ባለስልጣናትን በማናገር እንደዘገበው የንግግሩ ዋና አላማ ሸሽተው በየጫካው ውስጥ የሚገኙ የመዠንገርና የሸኮ ተወላጆች አሳምኖ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ነው። ይሁን እንጅ ለድርድር የሄዱ አንዳንድ የመዠንገር ተወላጆች መታሰራቸው ንግግሩን ተአማኒነት አሳጥቶታል።
አሁንም በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት በበብዛት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ግጭት ቢቆምም ውጥረቱ ግን እንዳለ ነው። መንግስት ለግጭቱ መንስኤ ናቸው የተባሉ የወረዳ ባለስልጣናት መያዛቸውን መግለጹ ይታወሳል።
በቅርቡ የመዠንገር ተወላጆች በፌደራልና በመከላከያ አባላት ላይ በወሰዱት ጥቃት ከ50 ያላነሱ ወታደሮች መገደላቸውን የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በሌላ ዜና ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊት አባል መጥፋት ጋር በተያያዘ በምእራብ አርማጭሆ የተያዘው ነርስ እርስቴ አለሙ ከፍተኛ አካላዊ ድብደባ ከደረሰበት በሁዋላ ተፈቷል።
የመንግስት ሰራተኛው ሲያምጽ፣ ወደ ህዝቡ ሊሸጋገር ይችላል በሚል ፍርሃት ግለሰቡ ለመፈታት መቻሉን የአንድነት ፓርቲ የዞኑ ሃላፊ የሆኑት አቶ አንጋው ተገኝ ገልጸዋል