ጥቅምት ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን በተመራውና ሁሉም የክልል መንግስታት የኮሚኒኬሽንና የመገናኛ ብዙሃኖች የተሳተፉበት የኢህአዴግ የምርጫ ዘመቻ ፕሮፓጋንዳ ዝግጅት ባለፈው ቅዳሜ ሲጠናቀቅ ሁሉም የክልል ሚዲያዎች ቀጣዩን ምርጫ ሊያሳምን የሚችል አቀራረብ ፣ ዜና እና ፕሮግራም እንዲየቀርቡ እንዲሁም በምርጫው የኢህአዴግ አሸናፊት ቅኝት ውስጥ ስራዎችን እንዲሰሩ ታዘዋል።
ብአዴን በምርጫው ዙሪያ ለከፍተኛ አመራሩ የሰጠውን ስልጠና ወደ መካከለኛ አመራሩ ያወረደ ሲሆን፣ መካከለኛ አመራሩም ከጥቅምት 10 እስከ 13 ምርጫውን በምን ሁኔታ ማሸነፍ እንደሚቻል ለመመካር በባህርዳር ከተማ ተሰብስቧል።
የብአዴን የዞን ድርጅት ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ሙሉዓዳም ጌታነህ ቀጣይ ጉዞአችንን ለማስቀጠል በምርጫው ውጤታማ እንድንሆን ተግተን እንሰራለን ያሉ ሲሆን፣ የመንግስት ሰራተኞች የብአዴን አባላት በተከታታይ እየሰበሰቡ “ብአዴንን በምርጫው እንዴት አሸናፊ ማድረግ ይቻላል?’ በሚለው ዙሪያ እንደሚመክሩ ታውቋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ከምርጫው ጋር በተያያዘ ትኩረት የሚያደርግባቸው ሰዎችና የመገናኛ ብዙሃንን የለየ ሲሆን፣ በቀዳሚነት የመንፈሳዊ ጉዳዮች ተመራማሪ፣ የማህበራዊ ጉዳዮች ተችና ጸሃፊ የሆነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከአገር እንዲወጣ ወይም የኢህአዴግን የልማት ስራዎችና ፖሊሲዎችን ደግፎ እንዲፅፍ ማድረግ እንደሚገባ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ስራዎችን እንደሚሰራ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በሰማያዊ ፓርቲ መሪ ኢንጂነር ይልቃል ላይ የተለያዩ ወንጀሎችንና ትችቶችን በመጻፍ ስማቸውን የማጥፋት ስራ መስራትና ከተቻለም ከአገር የሚወጡበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ይሰራል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስከ ምርጫው ፍጻሜ መታሰር አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን ኢሳት ቴሌቪዥንና ኢሳት ሬዲዮን ማፈን ተገቢ በመሆኑ የደህንነት መስሪያ ቤቱ የቀጣይ ስራው የትኩርት አቅጣጫ እንደሚሆኑ ምንጮች ገልጸዋል።
ሰሞኑን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርጫ ተኮር ተደርጎ የተሰጠው የፖለቲካ ስልጠናም በኢህአዴግ ፅ/ቤት እየተገመገመ ሲሆን፣ ” ልማት ከታሰበ ኢህአዴግ መፍረስ አለበት ” በማለት ሲናገሩ የነበሩ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ “የአማራ ተወላጅ” ተማሪዎች ” ትምክተኞች” የተባሉ ሲሆን፣ አማራ ዛሬም አዲስ ስርአት የሚናፍቅ ነው በሚል በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሚታዩ ስጋቶች ተርታ ተመድበዋል።
የትግራይ ክልል ተማሪዎች በመልካም አስተዳደር ላይ ምስጋና ማቅረባቸው ሲወደስ፣ የኦሮሞ ተማሪዎች ባለፈ ታሪካቸው የሚቆጩ፣ አሁንም ያንን ታሪክ በተቃራኒው ለመድገም ፍላጎት ያላቸው ናቸው ተብለዋል። በደቡብ ክልል በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የተደረገው ውይይት ” ጉራጌ አሁንም አኩራፊ ሆኖ እንደቀጠለ የሚያሳይ ነው ተብሎአል። ወላይታ ከትግራይ በመቀጠል አስተማማኝ ሲባሉ፣ ዳውሮ፣ ከምባታ፣ ስልጤ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሊ፣ ሀረሪና የመሳሰሉት ጠንካራ ፓርቲ ካገኙ ኢህአዴግን ሊከዱ የሚችሉ ናቸው ተብለዋል። ቤንሻንጉል ጉሙዝ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ለማክበር በሚገነባው መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ስለሚሆን የምርጫ ውጤት ማግኘት ይቻላል ሲል የግምገማ ሪፖርቱ አመልክቷል።
በግብረ መልሱ ስርም በዩኒቨርስቲዎች ጠንካራ አመራርና መምህራንን በመመደብ የምርጫ አስፈጻሚ ግብረሃይል በኢህአዴግ አጋዥነት ቢዋቀር አመጽን ለመቆጣጠር ይቻላል የሚል ሀሳብ ሰፍሯል።
የኢህአዴግ 20 በ80 የምርጫ እቅድ የመንግስት ሰራተኞች ከጊዜያቸው 80 በመቶውን ለምርጫ 20 በመቶውን ለመንግስት ስራ እንዲያውሉ ያዛል