መስከረም ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት ለቀናት ጋብ ብሎ የቆየው ግጭት ከትናንት ጀምሮ እንደገና አገርሽቷል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ
ጋትሉዋክ ቱት የገዢው ፓርቲ ልሳን ለሆነው ፋና ሬዲዮ ” ኪራይ ሰብሳቢዎችና የመሬት ደላሎች በጠነሰሱት ሴራ ለዘመናት ተቻችሎ የኖረውን ህዝብ ለመከፋፈል ጥረት በማድረጋቸው
መስከረም አንድ በሚጤ ከተማ በተፈጠረው ግጭት 13 ሰዎች” መሞታቸውን፣ በገጠር ቀበሌዎችም ተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ ቁጥሩ ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል። አቶ
ጋትሉዋክ የመሬት ደላሎች ያሉዋቸውን በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፣ ይሁን እንጅ ኢሳት የቀድሞ የህወሃት የጦር መኮንኖች በአካባቢው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እየገዙ የመዠንገር
ብሄረሰብ ተወላጆችን እያፈናቀሉ መሆኑ ለአሁኑ ግጭት መቀስቀስ ዋነኛው መንስኤ መሆኑን የአካባቢውን ሰዎች በማነጋገር መዘገቡ ይታወሳል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት ግጭቱ መብረዱንና የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ቢገልጹም ፣ ዛሬ ለኢሳት የደረሰው መረጃ ግጭቱ በገጠር ቀበሌዎች ካለፉት ሁለት ቀናት
ጀምሮ መቀጠሉንና በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ያመለክታል። በአካባቢው ኢንቨስትመንት የነበራቸው 2 የቴፒ ባለሃብቶች ትናንት መገደላቸውን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ የሞቱ
በርካታ ሰዎች አሁንም ጫካ ውስጥ ተጥለው እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።
ኢሳት ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይችልም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሟቾችን ቁጥር ከመቶ በላይ ያደርሱታል። እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት በርካታ አስከሬን በየጫካው ተጥሎ
ከመገኘቱም በላይ ታጣቂዎችን በመፍራት እስካሁን ለመሰብሰብ አልተቻላም።
መንግስት በቅርቡ የአካባቢውን የጸጥታ ሹም በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ ይታወቃል።
የአንዋ ሰርቫይቫል ዳይሬክተር አቶ ኒክ ኦቻላ፣ መንግስት ምርጫ ሲቀርብ ብሄረሰቦችን እርስ በርስ ማጋጨት የተለመደ ተግባሩ መሆኑን በመግለጽ ለግጭቱ መቀስቀስ መንግስትን
ተጠያቄ አድርገዋል። መንግስት የቀየሰው የመሬት ወረራ ፖሊስም ለግጭቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭቱ በቀላሉ ይፈታል ብለው
እንደማያምኑ ይናገራሉ።