መስከረም ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ ኒክ ኦቻላ ለኢሳት እንደገለጹት በኢትዮጵያ አዲስ አመት ደገኞች በፈጸሙት ጥቃት 8 የመዠንገር ተወላጆች ተገድለው ፣ ከ3 ሺ በላይ የሚሆኑት መሰደዳቸውን ገልጸዋል። 835 መዠንገሮች ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠግተው በምግብ እጥረትና በብርድ ሲሰቃዩ መቆየታቸውን አቶ ኒክ ተናግረዋል።
አቶ ኒክ እንደሚሉት ለግጭቱ መንስኤ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣው የመሬት ቅርምት ፖሊሲ ነው። በዚህ ፖሊሲ የተነሳ በርካታ መዠንገሮች አካባቢውን እየለቀቁ መሰደዳቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ደገኛ የሚባሉት ተወላጆች ከመዠንገሮች በደረሰባቸው ጥቃት መሰደዳቸውን እንዴት እንደሚያዩት የተጠየቁት አቶ ኒክ፣ “የማንም ሰው መፈናቀል ጥሩ ስሜት አይሰጠንም፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እስከሆንን ድረስ መቻቻልና መግባባት መኖር አለበት” ብለዋል። ገዢው ፓርቲ ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ነዋሪዎችን እርስ በርስ እንዲጋጩ ማድረግ የተመደ ስራው በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
መሬትን እየሸጠ ያለ መንግስት ነገ ከተጠያቂነት አያመልጥም ያሉት አቶ ኒክ፣ የመዠንገር ህዝብ ከመሬቱ ሲፈናቀል ችግሩ የኢትዮጵያ ችግር አድርገን በመውሰድ ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል
ባለፈው ሳምንት በክልሉ እንደገና ባገረሸው ግጭት ከ20 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሎአል። የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከቀያቸው ተፈናቀለው ሚጤ ላይ ሰፍረው የነበሩትን ሰዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸው ታውቋል።