መስከረም ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከክልሉ ባለስልጣናት የሚደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፕሬዚዳንቱ አቶ አብዲ ሙሃመድ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ ከጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ የቀረበላቸውን ጥሪ ባለመቀበል በክልላቸው የሚገኙ ሲሆን፣ ” በኢትዮጵያ ውስጥ ከህወሃቶች በስተቀር ማንም ከስልጣን ሊያነሳኝ የሚችል ሃይል የለም” በማለት፣ የአቶ ሃይለማርያምን ጥሪ ውድቅ አድርገዋል። በምስራቅ እዝ አዛዥ ጄ/ል አብርሃም ገብረማርያም እንደሚተማመኑ የገለጹት አቶ አብዲ፣ አቶ ሃይለማርያምን ጄኔራል ሳሞራ የሚሉትን የሚፈጽሙ በመሆናቸው ምንም እንደማያመጡ ተናግረዋል። የህወሃት ባለስልጣናት ድጋፍ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አብዲ፣ ለአቶ ሃይለማርያም ያላቸውን ንቀት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል። ህወሃቶች ፊታቸውን ቢያዞሩባቸው ክልሉን እንደሚገነጥሉ የሚዝቱት ፕሬዚዳንቱ፣ 7 የስራ አስፈጻሚ አባሎችን ካባረሩ በሁዋላ አዳዲስ ሰዎችን ለመሾም እየተዘጋጁ ነው።