ጳጉሜን ፬(አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከመከላከያ ሰራዊት የከዱ 10 የሚደርሱ
ወታደሮች ከሆሳእና ከተማ ባለስልጣናት ጋር የፈጠሩትን ውዝግብ ተከትሎ፣ አንድ
የከተማው የምክር ቤት አባል በደረሰበት ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣
ይህን ተከትሎ አንደኛው ወታደር ሲያዝ ቀሪዎቹ አምልጠዋል።
ይሁን እንጅ ወታደሩ ነሃሴ 30 ቀን 2006 ዓም ታይዞ መታሰሩን የገለጹት
ምንጮች፣ ያልተያዙት ወታደሮች በምሽት እስር ቤቱን በመስበር ባልደረባቸውን
አስፈትተው ማምለጣቸው ታውቋል።
በተለያዩ እዞች ውስጥ የነበሩት ወታደሮች በስርአቱ በመማር ጥለው መጥፋታቸውን
ምንጮች ገልጸዋል። ወታደሮቹ እስካሁን ያልተያዙ ሲሆን፣ የአካባቢው አስተዳደር
የጸጥታ ስጋት ፈጥረዋል በሚል ለመያዝ ጥረት እያደረገ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በአላባ ጠምባሮ ዞን 10 የከዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት
መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ በእስር
ቤት ውስጥ የሚገኙት ወታደሮች፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ መሆኑን
ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ አባላትን ማዋከቡ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን በተለያዩ
ስፍራዎች የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን ገልጸዋል። ተቀማጭነታቸው በጅንካ የሆኑት የኦሞ ህዝቦች
ዲሞክራሲያዊ ህብረት የዞኑ ጸ/ቤት የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዳዊት ታመነ ነሃሴ 26 ቀን
ወደ ዞኑ የፍትህና ጸጥታ ማስከበር ጽ/ቤት ተጠርተው ከፍተኛ ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል።
የጸጥታ ሹም የሆኑት አቶ ተስፋየ ጣሰው ወርቅነህ በፖሊሶች ታጅበው ” ሰዎችን እየቀሰቀስክ
ህዝቡ እንዳይታዘዝ አድርገሃል፣ ህዝቡን ለማሳመጽ እየሰራችሁ ነው፣ እናንተ በምታደርጉት
ቅስቀሳ የመንግስት መመሪያ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም” የሚሉ ክሶችን በአቶ ዳዊት ላይ
ካዥጎደጎዱ በሁዋላ፣ ከዚህ ድርጊታችሁ በፍጥነት የማትታቀቡ ከሆነ አስፈላጊውን እርምጃ
እንወስዳለን ብለው አስጠንቅቀዋቸዋል።
አቶ ዳዊት በበኩላቸው በሰላማዊ ትግል ስርአቱን ለመተካት እየታገሉ መሆኑንና እስካሁን
ድረስ ያደረጉት ትግልም ህገመንግስቱን ባከበረ መልኩ በመሆኑ፣ ከሚሰሩት የድርጅት ስራ
እንደማይታቀቡ ገልጸዋል። አቶ ዳዊት የሰጡት መልስ በዙሪያው የነበሩ ፖሊሶችን ሳይቀር
ማስገረሙን የገለጹት ምንጮች፣ በዚህ ድርጊት የተበሳጨው የጸጥታ ሹሙ፣ እርምጃ
እንደሚወሰድ በመዛት ላይ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
አቶሀብታሙቶልባ፣ አቶይርጋለም ገላዉ የተባሉ የአካባቢው ተወላጆችም እንዲሁ ከፍተኛ
ወከባ እንደደረሰባቸው ታውቋል።