ነሃሴ ፳፩(ሃያአንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኩሬበረት እና እምባይድ ቀበሌ የሚገኙ ነዋሪዎች እንደገለጹት ከአፋር አካባቢ የሚመጡ ማንነታቸው
ያልተወቁ ታጣቂዎች ንብረታቸውን በተደጋጋሚ እየዘረፉና ግድያም እየፈጸሙባቸው መሆኑን ተናግረው፤መንግስት ጉዳዩን ተከታትሎ የእርምት እርምጃ
አለመውሰዱ በግድያው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ማድረጉን ገልጸዋል።
ግድያ እና ዘረፋ ሲካሄድ ጥበቃ ከማድረግ ይልቅ “-ራሳችሁን ጠብቁ ፣ንብረታችሁን ጠብቁ እና ወደ ጫካ አትውጡ ” በማለት የሚሰጠው መልስ ግዴለሽነቱን
እያሳየን ነው በማለት ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ከክረምቱ መግቢያ አንስቶ እስከ ህዳር ወር ድረስ በየአመቱ በተደጋጋሚ የሚከሰት ቢሆንም ፣ ዘንድሮም
በተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው ያለምንም ከለላ መቀመጣቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አርሶአደሮች ወደ እርሻ ቦታ በመሄድ ስራቸውን ለመስራት የተቸገሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በእርሻ ማሳዎች ለመስራት የሚሄዱት በቀን
ለተወሰነ ሰዓት ሲሆን እርስ በርሳቸው ዙሪውን ጥበቃ በማድረግ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀንም ሆነ በምሽት ስጋት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮች በየጊዜው የሰው ነፍስ የሚጠፋበትና የንብረት ዘረፋ ሁኔታ እስከ መቸ ሊቆምላቸው እንደሚችል
ግራ የተጋቡ መሆኑን ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
መንግስት አለ ከተባለም አንደዚህ አይነት በደል በህዝቦች ላይ እየተፈጸመ ጀሮ ዳባ ማለት አይገባውም ሲሉ ለህዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ የወረዳ አመራሮች አስተያየታቸውን
ለዘጋቢያችን ሰጥተዋል፡፡
በአካባቢው ያለው ችግር የመንግስት ሹሞች ሆን ብለው የሚፈጥሩት ነው በማለት የአፋር ሰብአዊ መብቶች ሊቀመንበር አቶ ገአስ አህመድ ከወራት በፊት ለኢሳት
መግለጻቸው ይታወሳል።