የጠ/ሚንስትር ጽ/ቤት በሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ

ነሃሴ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት ኢህአዴግ ምንጮች እንደገለጹት በሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ኡመር እና

በክልሉ የካቢኔ አባሎች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ በጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት በተካሄደው አስቸኳይ ግምገማ ፣ ፕሬዚዳንቱ

ፈጸሟቸው የተባሉ በርካታ ወንጀሎች ተዘርዝረው ቀርበዋል።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በሰብሳቢነት በመሩት ግምገማ ላይ ም/ል ጠ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የጠ/ሚኒስትሩ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አለቃ ጸጋየ በርሄ፣

የደህንነት ምክትል ሹሙ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ፣ የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ጄኔራል አብርሃ በቅጽል ስማቸው ኳታር፣ የፌደራልፖሊስ ወንጀል መከላከል ሃላፊ

ጄ/ል ግርማየ መንጁስ፣  አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ አብዲ መሃመድና የተለያዩ የክልሉ የካቢኔ አባላት እንዲሁም ሌሎች 2 የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችም

ተገኝተዋል። አቶ አብዲ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ  እሳቸው በሚመሩት ሚሊሺያ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች  በተለያዩ ምክንያቶች መገደላቸውን፣ በርካታ

ሲቪሎች ታስረው ህክምና ሳይገኙ በቀላፎ፣ በፌርፌርና በሌሎችም እስር ቤቶች እንዲሞቱ ማድረጋቸው፣ ከመንግስት የተመደበውን ግዙፍ  በጀት ለአንዳንድ

የፌደራል ባለስልጣናት በተለይም ለጄ/ል አብርሃ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ ወቅቶች እንዲሰጣቸው በማድረግና በተለያዩ መንገዶች በብዙ መቶ

ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንዲዘርፍ ማድረጋቸው እንዲሁም ከ20 ቀናት በፊት የአገር ሽማግሌዎችን በመሰብሰብ በአንቀጽ 39 መሰረት የራሳችንን  መንግስት

ስለምናውጅ ለዚህ ታሪካዊ ክስተት ራሳችሁን አዘጋጁ፣ ፌደራል መንግስትም በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት አይችልም ብለው መናገራቸው፣ የልዩ ፖሊስና የጎሳ

አባላቱ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲዘርፉ ማሰማራታቸው፣ በክልሉ የሚካሄዱትን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ያለ ጫራታ በመስጠት ሆን ብለው ለብዝበዛ አዘጋጅተዋል የሚል

ግምገማ ቀርቦባቸዋል።

በግምገማው ወቅት ጄ/ል አብርሃ በአቶ አብዲ ላይ የቀረበውን ግምገማ አጥብቀው ተቃውመዋል። አቶ አብዲ ” ምነው መለስ በኖረ” የሚል ቃል ከመናገራቸው

ውጭ ምንም አይነት መልስ ሳይሰጡ ግምገማው ተጠናቋል። አቶ ሃይለማርያም የአቶ የአብዲን ተቀናቃኞች ሰብስበው ያነጋገሩ ቢሆንም፣ ስለሚወሰደው እርምጃ

ምንም ሳይሉ ቀርተዋል።

አቶ አብዲ ከደህንነቱ ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋና ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ  ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ አቶ ሃይለማርያም እርሳቸውን ለመገምገም ስልጣን

እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ሲነጋሩ ይሰማል። የአቶ አብዲ ጉዳይ የህወሃት ባለስልጣናትን ለሁለት መክፈሉ  ታውቋል።