ነሃሴ ፲፫(አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ ከታሰሩ በርካታ ወራትን ያስቆጠሩት የአገር ሽማግሌዎች
ፍትህ አጥተው እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጸዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ የወረዳ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በማንሳታቸው እና የጸጥታ ሃይሎች የሃይል
እርምጃ መውሰዳቸውን ለጠ/ሚኒስትሩና ለሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በማመልከታቸው መታሰራቸው ይታውቃል።
ከ400 ያማያንሱት እስረኞች ዛሬ ነገ እንፈታለን ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚችል ባለስልጣን አላገኙም።
የተወሰኑት የአገር ሽማግሌዎች ፍርድ ቤት ዛሬ ቀጥሮዋቸው የነበረ ቢሆንም፣ ዳኞች የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስልጠና ላይ ናቸው በሚል ጉዳያቸው ሳይታይ ቀርቷል።
በሌላ በኩል ግን ከፌደራል መንግስት ተላኩ አጣሪዎች ወደ ወረዳው በመሄድ ነዋሪዎችን አነጋግረዋል። አጣሪዎቹ በስፍራው ደርሰው ከተመለሱ በሁዋላ አንጻራዊ ሰላም
መስፈኑንም ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።