ነሃሴ ፲፪(አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመጣል ህዝቡን ያነሳሳሉ በማለት ክስ ከተመሰረተባቸው መጽሄቶች መካከል
አንዱ የሆነውን የፋክት መጽሄትን ጉዳይ ለማየት የተሰየመው የከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ፣ ስራ አስኪያጇ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ሌላ ቀጠሮ ለመስጠት ተገዷል።
ስራ አሰኪያጇ ወይዘሮ ፋጡማ ኑርየ ለምን ሳይቀርቡ እንደቀሩ የታወቀ ነገር የለም። ፖሊስ ተከሳሷ እንዲቀርቡ በስልክ መልእክት ማስተላለፉን ለፍርድ ቤት ገለጿል።
ፍርድ ቤትም ተከሳሷን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያመጣ ትእዛዝ ሰጧል።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ፋክት፣ ጃኖ፣ ሎሚ፣ አዲስ ጉዳይ፣ እንቁ መጽሔቶች እና አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ አሳታሚዎችና ድርጅቶች ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወቃል።
መጽሔቶቹ ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የዓመጽ ቅስቀሳና የሐሰት ወሬዎች በመንዛት ሕገ-መንግስታዊው ስርዓት በሃይል እንዲፈርስና ህዝቡ
በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ የወንጀል ተግባሮቻቸውን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን መንግስት ጠቅሷል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ግን እርምጃው ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ መወሰዱን ይገልጻሉ።