ሐምሌ ፴(ሠላሳ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ40 በላይ አፍሪካ መሪዎችን በአንድ ጊዜ ጋብዘው በማነጋገር ላይ ያሉት የአሜሪካው መሪ ፕ/ት ባራክ ኦባማ አፍሪካ እያደገችና ጠንካራ
አህጉር እየሆነች መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሳይሆን አፍሪካ በአለም ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን መጀመሩዋን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ስኬት ከወጣት ህዝቦቿ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
አሜሪካ በአፍሪካ የጸጥታ ስራ ለመስራትና ለኢንቨስትመንት 14 ቢሊዮን ዶላር መመደቡዋን አስታውቀዋል። ይህ ገንዘብ ቻይና በአፍሪካ ኢንቨስት ካደረገቸው ጋር ሲተያይ እጅግ አነስተኛ
መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ። የአሜሪካ ዋና ፍላጎት ቻይና በአፍሪካ ላይ እየፈጠረችው ያለውን ተጽእኖ መቀነስ መሆኑን የሚገልጹት ተንታኞች፣ አሜሪካ ለረጅም ጊዜ ይዛ የቆየችውን
” የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች” መስፈርትን ወደ ጎን በማለት ከአንባገነን የአፍሪካ መሪዎች ጋር ቀረቤታ መፍጠሩዋ፣ በቀሪው አፍሪካ ህዝብ ዘንድ ሊያስጠላት እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
ቻይና በአፍሪካ ከፍተኛ ኢነቨስትመንት ቢኖራትም፣ የህዝብ ተቀባይነት እንደሌላት ለዚህም ዋና ምክንያቱ በሙስና ከተዘፈቁትና ከአንባገነን መሪዎች ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ነው ይላሉ።
ፕ/ት ኦባማ በመጨረሻው ጉባኤ በመልካም አስተዳደር እና በጸጥታ ዙሪያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡