ሐምሌ ፲፰(አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሳምንታት በፊት እስራኤል በሃመስ የሚወነጨፉ ሮኬቶችን ለማውደምና መሬት ለመሬት የተሰሩ መተላለፊያዎችን ለመዝጋት በሚል ምክንያት
ጦሯን ወደ ጋዛ መላኩዋን ተከትሎ፣ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እየደረሰ ነው። እስካሁን ድረስ ከ800 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል። የተባበሩት መንግስታት
ድርጅት እንደሚለው አብዛኛው ሟቾች ህጻናትና ሴቶች ናቸው። በእስራኤል ወገን ደግሞ 35 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ከ2 ቱ በስተቀር ሌሎች ወታደሮች ናቸው። እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃማስ ወታደሮችን
መግደላን እንዲሁም ወደ እስራኤል የሚያስገቡ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ቦዮችን ማውደሟን ገልጻለች።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው ድርጊት አለማቀፍ ውግዘት ቢያስከትልባትም፣ እስራኤል በበኩሏ ለህጻናትና እናቶች ሞት ሃማስን ተጠያቂ ታደርጋለች።
ግጭቱ ተባብሶ በቀጠለበት ቢዘህ ወቅት፣ አሜሪካ፣ ግብጽና እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም ለማውረድ እየተንቀሳቀሱ ነው። እስራኤል የዘረጋችው ከበባ የሚያቆም ከሆነ ሃማስ የተኩስ
አቁም ስምምነት ለማድረግ እንደሚፈልግ መሪዎች ተናግረዋል። እስራኤል በበኩሏ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ለማፍረስ ሲባል ጦሯ ጋዛን ለቆ እንደማይወጣ አስታውቃለች። የተባበሩት መንግስታት
ድርጅት የተስፋ ጭላንጭል እንዳለ እየገለጸ ቢሆንም፣ ጦርነቱ በምን መልኩ እንደሚቆም የሰጠው ፍንጭ ግን የለም።