ሐምሌ ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ እና የጋራ ብልጽግና መስሪያ ቤት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ማርክ ሲሞንድ የግንቦት7 ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣
ከእንግሊዝ መንግስት የኮንሱላር ምክር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚጠይቅ ደብዳቤ ለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጽፈዋል። ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሰጠው መልስ፣
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ የተባለ ድርጅት መሪ መሆናቸውን ገልጾ፣ አሸባሪ ለመሆናቸው ማሳያ ይሆን ዘንድ ግንቦት7 በቅርቡ ያወጣውን መግለጫ በእንግሊዝኛ ተርጉሞ አያይዞ
አቅርቧል። ግንቦት7 አቶ አንዳርጋቸውን ለማስፈታት በኢትዮጵያ ፣ በየመን እና በእንግሊዝ መንግስታት ላይ ኢትዮጵያውያን መውሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች የሚዘረዝር መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል።
በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በእንግሊዝ ኢምባሲ ፊት ለፊት በመሄድ ተቃውሞ እንዲያሰሙ፣ ተከታታይ ደብዳቤዎችን እንዲጽፉ የሚጠይቀውን መግለጫ፣ ግንቦት7 አሸባሪ ድርጅት ለመሆኑ
ማሳያ ነው በማለት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የጻፈው ደብዳቤ የፓርላማ አባላቱንና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኞችን እንዳስገረማቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የአቶ አንዳርጋቸው
ቤተሰቦች ገልጸዋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉት ሁለቱ የፓርላማ አባላት ጀርሚ ኮርቢን እና ኤምሊ ቶርንቤሪ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሰጠው መልስ ከተገረሙት መካከል ሲሆን፣
ባለስልጣኖቹ የእንግሊዝ መንግስት በሂደት ስለሚወስደው እርምጃ እንዲብራራላቸው ደብዳቤ ጽፈዋል። የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሃፊ፣ አገራቸው በተከታታይ ስለምትወስደው እርምጃ ዝርዝር
መርሃ ግብር እያዘጋጁ መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ገልጿል።
ኢሳት ባለስልጣኖቹ የተጻጻፉዋቸው ደብዳቤዎች ቅጅ የደረሰው ሲሆን፣ ከደብዳቤዎች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ መንግስት በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የሚያቀርበው የሽብርተኝነት ክስ ግንቦት 7 መንግስትን
በሃይል አወርዳለሁ ብሎ ማወጁ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ አሁንም የመነጋጋሪያ አጀንዳ እንደሆነ ቀጥሎአል። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች ስልኮችን ለኢሳት በመደወል ለአቶ አንዳርጋቸው ያላቸውን
አክብሮትና መካሄድ ስላለበት ትግል አስተያየቶችን ይሰጣሉ።