ሐምሌ ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ የጸጥታ ሃይሎች የአንድነት ፓርቲን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነውን ወጣት ሃብታሙ አያሌውን ፣ የፓርቲውን የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆነውን የሽዋስ አሰፋን እንዲሁም በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን ከመቀሌ በመጻፍ የሚታወቀውና አረና ፓርቲ አባል የሆነው መምህር አአብራሃ ደስታን ይዞ አስሯል።
እሰረኞቸ ማእከላዊ በሚባለው ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። አንደነት ባወጣው መግለጫ “የሰብአዊ መብት ረገጣና ድፍጠጣ በእጅጉ ተባብሶ ወደ መንግሥታዊ የውንብድናና ጥቃት መቀየሩን ፤ ዜጎች መንግሥት እንዳሰማራቸው የምንጠረጥራቸው የደህንነት ኃይሎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በጅምላ መታሰራቸውን ፣ መደብደባቸውንና በስውር እስር ቤቶች ተወርውረው ደብዛቸው እንዲጠፋ መደረጉን ” ገልጿል።
ይሄው እስር እንደ ተለመደው የተቀነባበረ የስርዓቱ ድራማ ከመሆኑም በተጨማሪ የ2007ን ሀገራቀፍ ምርጫ በተለመደው ማሸማቀቅና ማወናበድ ለመውሰድ የተጀመረ የመጀመሪያ ርምጃ ነው ብለን እናምናለን ሲል ፓርቲው አስታውቋል።
ፓርቲው “ፓርቲያችን አንድነት አባላትንና አመራሮቻችንን በማሰቃየትና በማሸማቀቅ ፣ በመደብደብ የአካል ማጉደል ጉዳት በማድረስ የሚያደርገውን አስነዋሪ ተግባር እያወገዘ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌው ፤ አቶ ዳንኤል ሺበሺና ሌሎችም በፖለቲካ አመለካከታቸውና እምነታቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ፖለቲከኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና ሳስባለን ፡፡ ሲል አክሏል።
በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ፓርቲዎችም ይህን ህገ ወጥ እስር በማውገዝ እንዲሁም ኢ-ፍትሀዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገውን ሩጫ በመቃወም እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲቆሙ ይህንን ህገ-ወጥነት በህዝባዊንቅናቄ ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።