ሰኔ ፴(ሠላሳ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የየመን የጸጥታ ሃይሎች የግንቦት7 ዋና ጸሃፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አሳልፈው በሰብአዊ መብት ጥሰትና ህዝብን በማሰቃየት በአለም የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ዘወትር ለሚወገዘው ለኢህአዴግ የጸጥታ ሃይሎች አሳልፈው መስጠታቸው ያበሳጫቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የነጻነት ትግሉን የምንቀላቀልበትን” መንገዱን ምሩን” በማለት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የተቃውሞ ሰልፎችን እያዘጋጁ ነው።
ለኢሳት ስልኮችን እየደወሉ ቁጣቸውን የሚገልጹት ኢትዮጵያውያኑ ፣ አንዳርጋቸው በነፍሳቸው የከፈሉትን መስዋትነት እነሱም ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ትግሉን ለመቀላቀል መንገዱ እንደጠፈባቸው ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ አመራሩን ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ይጠይቃሉ።
ግንቦት7 ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓም ባወጣው መግለጫ ትግሉ “ሁላችን አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ወደ ተባለ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጿል።
አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ልክ እንደሱ ትሁት ሆኖ ግን ቆራጥ፤ ሆደ ሰፊ ሆኖ በዚያው ልክ ደግሞ መራር፤ አስተዋይና ብልህ ሆኖም ተግባር ተኮር መሆን ማለት ነው ብሎአል።
አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ወያኔን ለማስወገድ መደረግ የሚገባውን እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀ ሰው እንዲሁም ለአገርና ለትውልድ ቤዛ መሆን ማለት ነው የሚለው የግንቦት 7 መግለጫ፣ አገዛዙ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ካተኮረባቸው ምክንያቶች አንዱ የወያኔን የዘር ፓለቲካና ፕሮፖጋንዳ በሚያመክን መልኩ በተግባር ትግል ውስጥ ካሉ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ እና ሌሎች ዘውግ ተኮር ድርጅቶችና ንቅናቄዎች ጋር ተግባራዊ ትብብር ማድረግ የሚችሉበት ደረጃ ድረስ ማቀራረብ በመቻሉ መሆኑን ገልጿል።
ንቅናቄው “አገዛዙን ለመጣል ትልቁን ድርሻ የሚያበረክተው ሕይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ፡ ከቁም ውርደትና ባርነት ለነጻነትና ለፍትህ ከወያኔ ጋር ጉረሮ ለጉረሮ እየተናነቁ እየጣሉ ለመውደቅ ፤ መስዋእት ለመሆን በወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንና የህዝብ ሃይሎች የሚያደርጉት ተግባራዊ እንቅስቅሴ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጠይቋል።
በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የተቃውሞ ሰልፎችን እያዘጋጁ ነው። በካናዳ ኦታዋ ማክሰኞ በብሪቲሽ ከፍተኛ ኮሚሽን መንገድ ከ1 ፒም ጀምሮ ይካሄዳል። በነገው እለት በተለያዩ ከቶሞች የሚደረጉት ሰልፎች ዋነኛ አላማቸው ምንድንነው በማለት ካስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑትን አቶ ውሂብ የሽጥላን አነጋገረናቸዋል
ከአሁን በሁዋላ እያንዳንዱ ፍትህ ወዳድ ኢትዮጵያዊ በዚህ ወሳኝ ወቅት ልዩነትን በማጥበብ በአንድነት ቆሞ የህግ የበላይነትን በሀገራችን ለማስፈን በመፋለም ታማኝነትን ማሳየት ይጠበቅበታል ሲልራዲዮ ነጃሽ አስታወቀ