ብአዴን ለመጪው ምርጫ ዝግጅት በሚል በተለያዩ የአማራ ክልሎች እያካሄደ ባለው ውይይት የአዊ ዞን ነጋዴዎችና ነዋሪዎች መንግስት በየጊዜው በሚያወጣው መመሪያ መሰላቸታቸውንና ቤት አፍርሱ በመባላቸው ለችግር መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በውጭአገራት ለረጅም አመታት ኖራ፣ በአነገሯ ኢንቨስት እንድታደርግ ተጠይቃ ወደ አገሯ የገባች ነዋሪ ፣ ወደ አገሯ ከመግባቱዋ በፊት ሲነገራት የነበረው ማግባቢያና ወደ አገሯ ከተመለሰች በሁዋላ በአካል ያየችው ነገር እንደተለያየባት ገልጻለች። ” በአገርሽ ላይ አትሰሪም በሉኝና የማርፍበት አገር ካለ ሸኙኝ” በማለት በምሬት የተናገረችው ነዋሪ፣ መንግስት ከቤት ጋር በተያያዘ በየጊዜው በሚያወጣው መመሪያ ለኪሳራ መዳረጉዋን ተናግራለች።
” በ15 ቀናት ሁሉንም ነገር አፍርሱ እንባላለን” በማለት የተናገሩት አንድ ነጋዴ፣ “ባለስልጣኖቹ በየጊዜው በሚወስዱት ያልተጠና እና እንደ ዶዘር ሁሉንም በሚደፈጥጥ እርምጃ” ስሜታቸው መጎዳቱን አስረድተዋል
“ጥቃቅን እና አነስተኛ የሚባለው ነገር ሲመጣ የመጀመሪያው ሰልጣኝ ነበርኩ” ያለው ሌላው ነዋሪ፣ መንግስት ቃል የገባውን ገንዘብ ለማበደር ባለመቻሉ፣ እርሱና ቤተሰቦቹ ለችግር መዳረጋቸውን ገለጾ፣ ይባስ ብሎ የስራ ቦታህን ትለቃለህ በመባሉ እርሱና ቤተሰቦቹ ለችግር ማደረጋቸውን ገልጿል። ውይይቱን ያካሄደው የአዊ ህብረተሰብ አስተዳደር ዞን ከከተማ ልማት እና ኢንዱስትሪ መምሪያ ጋር በመሆን ነው።
ተመሳሳይ ውይይቶች በሌሎች አካባቢዎች እየተካሄዱ ሲሆን በቅርቡ በደብረብርሃን በተካሄደው ውይይት ነዋሪው የመብራት እና የመንገድ ችግሮችን በተደጋጋሚ ማንሳቱ ተዘግቧል።