ሰኔ ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ የሲቪል ሰርቪስ ቀንን በማስመልከት ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ከሃምሌ 1 ቀን 2006 ኣ.ም እንደሚደረግ ሲገልጹ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጡረተኞችን ጭማሪው ስለ መመልከቱ አለመነገሩ እንዳሳሰባቸው አንዳንድ ያነጋገርናቸው ጡረተኞች ገለጹ፡፡
በአጼው ዘመነ መንግሥት ሰዎች በስራ ላይ እያሉ ጉልበታቸው ሳይደክም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በቀላሉ ያገኙ ስለነበር ጡረታ ሲወጡ እሱን በማከራየት ወይንም በመሸጥ ኑሮአቸውን ስለሚደጉሙ ብዙም ችግር አያገኛቸውም ነበር ያሉት አንድ ጡረተኛ በደርግ እና በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመናት ግን ይህ በመጥፋቱ ጡረተኛው በአነስተኛ ገቢ የሰቆቃ ሕይወት እየመራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለመንግስት ሠራተኛው ቢያንስ በአምስት ኣመት አንድ ጊዜ ጭማሪ ሲደረግ ጡረተኛው እንደሚረሳ ጠቁመው እነዚህ ጡረተኞች ግን ለሀገር አገልግለው የተሰናበቱ በመሆኑ ሊረሱ አይገባል ነበር ብለዋል፡፡ለጡረተኛው እስከ 60 በመቶ የሚሆን ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገው በ2000 ዓ.ም አካባቢ እንደ ነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው ሆኖም ፣ ጭማሪውን ግን የዋጋ ንረት ብዙም ሳይቆይ እንደበላውና የጡረተኛው ኑሮ ተመልሶ ወደ ሰቆቃ እንደተዘፈቀ አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአብዛኛው ጡረተኛ ወርሃዊ ገቢ ከ500 ብር በታች መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ገንዘብ ቤተሰባቸውን ማኖር ያልቻሉ በርካታ ጡረተኞች ለጎዳና ተዳዳሪነት፣ለልመና እና ለእምሮ ቀውስ ተዳርገው በየሜዳው ወድቀዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ 630 ሺህ በላይ ጡረተኞች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ ከ150 ሺህ በላይ ጡረተኞች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡