ሰኔ ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሶስት ቀናት በፊት የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ታጣቂዎች በደጋሃቡር ላይ ድንገት በፈጸሙት ጥቃት ከሞቱት 7 የመንግስት ታጣቂዎች በተጨማሪ የደጋሃቡር የጸጥታ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት አቶ አሻር ፣ በታጣቂዎች ጥይት ቆስለው ወደ ደጋሃቡር ሆስፒታል ከተወሰዱ በሁዋላ ዛሬ ጠዋት ሰኔ 17 ቀን 2006 ዓም ማረፋቸውን የደረሰን ዜና አመልክቷል።
የአካባቢው የልዩ ሚሊሺያ አዛዥ የሆኑት ሙሃመድ ዳይክ ክፉኛ ቆስለው አሁንም በሆስፒታሉ በመታከም ላይ ሲሆኑ፣ አማጽያኑ ጥቃቱን ፈጽመው ከአካባቢው መሸሻቸው ታውቋል።
ኢህአዴግ በክልሉ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ላይ መጣሉን ተከትሎ ከኦብነግ ጋር ሊያደርገው ያሰበው ድርድር ሁለት የኦብነግ አመራሮች ናይሮቢ ኬንያ ላይ ተይዘው ከተወሰዱ በሁዋላ ተደናቅፏል። መሪዎቹ እጃቸውን በፈቃዳቸው እንደሰጡ መንግስት ቢገልጽም፣ እስካሁን ድረስ የታፈኑት መሪዎች ቀርበው እጃቸውን በፈቃዳቸው መስጠታቸውንና አለመስጠታቸውን አልተናገሩም።
በአካባቢው እየታየ ያለው ሁኔታ ያሰጋው መንግስት የክልሉን ፕሬዚዳንት ለመተካት ውስጥ ውስጡን እንቅስቃሴ ቢጀምርም፣ በአካባቢው የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች የፕሬዚዳንቱን መተካት በመቃወማቸው በመንግስት ሹሞችና በመከላከያ አዛዦች መካከል ልዩነት ተፈጥሮአል። በመንግስት በኩል ያለው አቋም ፕሬዚዳንቱ አቶ አብዲ ሞሃመድ ኡመር በሚከተሉት ፖሊሲ የክልሉ ህዝብ ይበልጥ እየተከፋ ተቃዋሚዎች ደጋፊ እየሆነ ነው የሚል ሲሆን፣ በመከላከያ አዛዦች በኩል ያለው አቋም ደግሞ አቶ አብዲ ለክልሉ ጸጥታ እና መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ናቸው የሚል ነው። ታዛቢዎች እንደሚሉት በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ኢንነቨስተር በመሆን እየሰሩ ያሉት የሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ገ/መስቀል የፍቅር ጓደኛ አቶ አብዲን በስልጣን ላይ መቆየት በእጅጉ ይደግፋሉ። ከመከላከያ ባለስልጣናት ጋር የተፈጠረው ከፍተኛ የሙስና ግንኙነት አቶ አብዲ የአካባቢውን የመከላከያ አዘዦች ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።
ሰሞኑን አቶ አብዲ 1500 በክልሉ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስበው የማእከላዊ መንግስት ባለስልጣናት በተለይም የደህንነት ሃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ ሊያስገድላቸው እንደሚፈልግ በግልጽ ሲናገሩ ተሰምቷል።
አብዛኛውን አገር ሽማግሌዎች ባስደነገጠ መልኩ፣ መንግስት እኛን ሳይሆን መሬታችንን ነው የሚፈልገው ያሉት አቶ አብዲ፣ የክልሉ ሽማግሌዎች የመንግስትን የደህንነት ሃይሎች እንዳይፈሩ መክረዋል። የደህንነት ሃይሎች ከክልላችን ተጠራርገው ወጥተዋል በማለት የተናገሩት ሹሙ፣ የደህንነት ሹሙም በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጅጅጋ የሚገኘው የነርሲንግ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ተሰብሳቢዎች ለ10 ቀናት ያክል እንዲያርፉበት የተደረገ ሲሆን፣ አቶ አብዲ አገር ሽማግሌዎች ከእርሳቸው ጎን እንዲቆሙ ከመማጸን ጀምሮ ፣ ክልሉን ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉ ሃይሎች ካሉ አንቀጽ 39ን ተግባራዊ እስከማድረግ እንደሚደርሱ ሲዝቱ መሰማቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአገር ሽማግሌዎችን ድጋፍ ለማግኘት በሚመስል መልኩ አቶ አብዲ ለእያንዳንዱ የአገር ሽማግሌ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲሰጣቸው አድርገዋል።
የግቢያቸው የጸጥታ አጠባባቅ ከወትሮው በተለየ እንዲጨምር መደረጉንና የሚጠራጠሩዋቸውን ጠባቂዎች ማባረራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አቶ አብዲ ሙሃመድ አማራ እና ኦሮሞ ምንጊዜም ሊታረቅ የማይችል በመሆኑ የሶማሊ ክልል ህዝብ ከትግራይ ጎን እንዲቆም የተናገሩበት የቪዲዮ ማስረጃ በኢሳት መለቀቁ ይታወሳል።