ግንቦት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሃረር ወኪላችን እንደዘገበው ለወባ መከላከያ በሚል ከውጭ በእርዳታ ስም የተገኘውን አጎበር የመንግስት ባለስልጣናት በአንድ ለአምስት እና በአንድ ለሰላሳ ላልተደራጁት አንሰጥም በመላታቸው ፣ መደራጀት ያልቻሉ ነዋሪዎች አጎበር ሳያገኙ ቀርተዋል።
በነጻ የሚታደለው ይህ አጎበር ከክረምቱ መግቢያ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ህዝብ ራሱን ከወባ እንዲከላከል ተብሎ የሚሰጥ ነው። ከአለማቀፉ የወባና ኤድስ ፈንድ በነጻ እንደተገኘ በሚገለጸው እርዳታ ፣ ገዢው ፓርቲ ዜጎች የድርጀቱ አባል ካልሆኑ አጎበር አይሰጣችሁም ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን አጎበር እንዳያገኙ የተከለከሉ ሰዎችን አነጋግሮ ዘጋቢያችን ሪፖርቱን አጠቃሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ የንግድ ድርጅቶቻቸው ለተቃጠለባቸው ሰዎች በሚሰጠው እርዳታ ላይ አድልዎ በመታየቱ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው።
ዜጋን ከዜጋ የመለየቱ ተግባር ተገቢ አይደለም የሚሉት ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሹሞች ሆን ብለው በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አላስፈላጊ አለመተማመን እንደፈጠርና እንዲጋጩ ለማድረግ መሆኑን ነጋዴዎች ገልጸዋል።
ከ1 ሺ በላይ ነጋዴዎች አሁንም ምንም አይነት መፍትሄ ያልተሰጣቸው ሲሆን፣ ስራ ለመጀመር ባለመቻላቸው ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ ወድቀዋል።