መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ሲጀመር ባለፉት ተከታታይ ቀናት ለውይይት ቀርቦ የነበረውን ሪፖርት ያለምንም ተቃውሞ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ በሞት የተለዩትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳን ለመተካት አዲስ ፕሬዚዳንት የሚመርጥ ሲሆን፣ ካፒታል የተባለው በአገር ውስጥ የሚታተመው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ቀድም ብሎ በሰበር ዜና የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ፕሬዚዳንት ሆነው እንደሚሾሙ ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጅ የኢሳት የክልሉ ምንጮች ” ወ/ሮ አስቴር የክልል ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸውና በክልሉ ህገመንግስት መሰረት አንድ ፕሬዚዳንት ለመመረጥ የግድ የክልሉ ምክር ቤት አባል መሆን አለበት ስለሚል ወ/ሮ አስቴር ከተመረጡ የክልሉ ህገመንግስት ሙሉ በሙሉ ይጣሳል” ብለዋል። ምንም እንኳ ሁሉም የክልሉ ምክር ቤት አባላት የኦህዴድ አባላት በመሆናቸው ህጉ ተጣሰ ብለው ጥያቄ ያነሳሉ ተብሎ ባይጠበቅም፣ ወ/ሮ አስቴር ከተሾሙ የክልሉ ህገመንግስት የየስሙላ መሆኑን እንደሚያሳይ ምንጮች ተናግረዋል።
የኦህዴዱ ሊቀመንበር አቶ ሙክታር ከድር የክልል ምክር ቤት አባል ቢሆኑም ፕሬዚዳንት ለማድረግ ችግር መፍጠሩንም ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ ሙክታር የምክትል ጠ/ሚኒስትርነቱን ስልጣን ትተው የክልሉ ፕሬዚዳንት ለመሆን ከወሰኑ ኦህዴድ በፌደራል ደረጃ ያለውን ውክልና የሚያሳጣ በመሆኑ፣ እርሳቸውን ወደ ክልል የማምጣት ፍላጎት አለመታየቱን ምንጮች ይናገራሉ።
አስገራሚው ነገር ይላሉ ምንጮች እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የ እጩ ፕሬዚዳንቶች ስም ለምክር ቤት አባላት አልተገለጸላቸውም። የምክር ቤት አባላቱም የተሰጣቸውን ስም አጽድቁ ሲባሉ ማጽደቅ እንጅ፣ የግለሰቡን ጠንካራና ደካማ ጎን ፈትሸው አስተያየት መስጠት አይፈቀድላቸውም።
ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አዲሱ የኦሮምያ ፕሬዚዳንት ይፋ አልተደረገም።