መጋቢት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የአትክልት ዘይት ሙሉ በሙሉ ከገበያ ጠፍቷል ማለት እንደሚቻል ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ስኳር እና የተለያዩ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች እጥረት መከሰቱን ተከትሎ፣ የእቃዎች ዋጋም እየናረ ነው። የአንድ ሊትር ዘይት የመሸጫ ዋጋ ከ25 ብር ወደ 35 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 45 ብር መሸጥ መጀሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በአንድ ለአምስት ካልተደራጁ በስተቀር በቋሚነት የማይገኘውና በኮታ ከአንድ ኪሎ በላይ የማይታደለው ስኳርም እንደ ዘይት ሁሉ ከገበያ እየጠፋ ነው።
የአትክልት ዘይት ዕጥረት ከማጋጠሙ ባለፈ ፣ በውድ ዋጋ የሚገዙት ዘይትም ቢሆን በጤናቸው በተለይ በወገብ እና መገጣጠሚያቸው ላይ ህመም እያደረሳባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡ አንዳንድ ሆቴሎች ምግብ ያለዘይት እስከ ማዘጋጀት መድረሳቸውን የከተማዋ ነዋሪዎችና የምግብ ቤት ባለቤቶች እንደሚናገሩ የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጻለች።
መንግስት የዘይት እጥረት ማጋጠሙን አምኖ ከውጭ በመግባት ላይ በመሆኑ ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀረፋል ብሎአል። ይሁን እንጅ ነዋሪዎች እንደሚሉት በባህርዳር እጥረት ካጋጠመ አንድ ወር የሞላው ሲሆን በሌሎች ከተሞች ደግሞ ከስድስት ወራት በላይ አስቆጥሯል። የስኳር እጥረት ካጋጠመም አመት ማስቆጠሩንና የእትረቱ ምክንያት ምን እንደሆነ እንደማያውቁ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።