የካቲት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አለምነው መኮንን በአማራው ህዝብ ላይ ያዘነቡትን ጸያፍ ስድብ ተከትሎ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባው ብአዴን፣ በክልሉ ፕሬዚዳንት በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በራሳቸው በአቶ አለምነው መኮንን እንዲሁም በብአዴን ሊቀመንበርና በምክትል ጠ/ሚንስትር ደመቀ መኮንን አማካኝነት መግለጫ ቢሰጠም፣ ህዝቡን ለማሳመን ባለመቻላቸው፣ በወቅቱ በስብሰባው ላይ የተገኙ ጋዜጠኞችና ሌሎች ተወያዮች ቀርበው አቶ አለምነው አልተናገሩም እያሉ እንዲያስተባብሉ እየተደረገ ነው።
ከአስተማማኝ የደህንነት ምንጮች በተገኘው መረጃ መሰረት ደግሞ መረጃውን ለኢሳት ያቀበሉትን ሰዎች ለማወቅ በወቅቱ የነበሩትን ጋዜጠኞች፣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና የደህንነት ሰራተኞች ስልክ በመጥለፍ ተጨማሪ ክትትል እያደረጉ ነው። ይሁን እንጅ መረጃው አስቀድሞ የደረሳቸው የደህንነት ሰዎች ማንኛውንም በስልክ የሚያደርጉትን ግንኙነት በማቆማቸው የተፈለገው ውጤት ሊገኝ ባለመቻሉ ተጨማሪ ራስ ምታት መፍጠሩ ታውቋል።
አቶ ደመቀ መኮንን ተቃዋሚዎች ልማቱን ለማደናቀፍ የፈጠሩት የኮምፒዩተር ቅንብር ነው ቢሉም የብአዴን አባላት ሳይቀሩ በሊቀመንበሩ ንግግር መበሳጨታቸውን ለኢሳት ተናግረዋል። በሚቀጥለው አርብ በሚደረገው የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጉዳዩ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
አንድነትና መኢአድ በባህርዳር ያደረጉት የተቃውሞ ሰልፍና ለተቃውሞ የወጣው ህዝብ ብዛት ያስደነገጣቸው የብአዴን አንዳንድ አመራሮችና አባላት፣ አቶ አለምነው በይፋ ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቁና ይህ ምእራፍ ይዘጋ በማለት እየጠየቁ ሲሆን፣ ዋናዎቹ አመራሮች ግን ጉዳዩ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ከመሆን አይዘልም በማለት የሌሎችን አስተያየቶች ሊቀበሉ ፈቃደኞች አልሆኑም።