የካቲት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በታህሳስ 2006 መጨረሻ የኢትዮጵያ ፕሬስ እና የኢትዮጽያ ዜና አገልግሎት ድርጅቶች ያጠኑትና ሰባት የግል መጽሔቶች ላይ ያተኮረ ጥናት ይዘት ላይ የሚወያይና ከፍተኛ የመንግስት ባለልጣናት የሚገኙበት ለጋዜጠኞች የተዘጋጀ ስብሰባ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በአዳማ እንደሚካሄድ ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የመንግስት ድጋፍ ያላቸው የጋዜጠኛ ማህበራት ከመንግስት የኮምኑኬሽን ጽ/ቤት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት በተነገረለት ስብሰባ ላይ ከ100 በላይ የመንግስትና በገዥው ፓርቲ ደጋፊነት የሚፈረጁ የግል ጋዜጦች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ላይ አወዛጋቢ የሆነውና በታህሳስ ወር 2006 መጨረሻ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ ይፋ የተደረገው የሰባት መጽሔቶች የአዝማሚያ ጥናት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎአል፡፡
የአዲስዘመን ጋዜጣ አሳታሚ የሆነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና እና በህግ በፈረሰ ስም እስካሁን የሚጠቀመውና በመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ስር አንድ መምሪያ ሆኖ የተዋቀረው የኢትዮጽያ ዜና አገልግሎት ድርጅት አጥንተነዋል ባሉት የአዝማሚያ ጥናት መሰረት አዲስ ጉዳይ ፣ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ዕንቁ እና ሊያ የተባሉ መጽሄቶች ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30/2006 ዕትሞቻቸው የፖለቲካ ስርኣቱን የሚያጨልሙ፣ የአመጽ ጥሪዎችን የሚያቀርቡ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያጥላሉ፣ ህገመንግስቱን የሚያዋድቁ፣ የመንግስት ባለስልጣናትን የሚያጥላሉ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታእና የመሳሰሉት ዘገባዎችን ማቅረባቸውን አጥኚዎቹ ማረጋገጣቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ጥናት መንግስት በቀጥታ በፕሬሶቹ ላይ ለመውሰድ ያሰበው እርምጃን ሕጋዊነት ለማላበስ የተዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ ከፍተኛ ትችቶች ሲቀርቡበት ቆይቷል።
በዚህ ሳምንት ዓርብ እና ቅዳሜ በአዳማ ይካሄዳል የተባለው ስብሰባ ምናልባት ወደቀጣይ ሳምንት ሊራዘም እንደሚችል የጠቀሱት የመንግስት ምንጮች፣ እስካሁን ባለው መረጃ ስብሰባው በዚህ ሳምንት ይካሄዳል የሚል ነው፡፡
በስብሰባው ላይ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በፕሬሶቹ ላይ የተካሄደው ጥናት ትክክለኝነት ለጋዜጠኛው ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል