ብአዴን ባህርዳር ላይ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይሳካ ለማድረግ የቀየሰው ስትራቴጂ ሳይሳካ መቅረቱን የውስጥ ምንጮች ገልጹ

የካቲት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አለምነው መኮንን የአማራን ህዝብ መዝለፋቸውን ተከትሎ አንድነት ፓርቲና መኢአድ የጠሩተን ሰልፍ ለማደናቀፍና ህዝብ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝ የተቀየሰው ስትራቴጂ ሳይሳካ መቅረቱን የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የሚገኘው ብአዴን ሰላማዊ ሰልፉን ለማጨናገፍ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች አንዱ በአንጻራዊነት የተሻለ ተሰሚነት ያላቸውን ወደ አዲስ አበባ ከመጡት የክልሉን ተወላጅ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮችን መካከል መርጦ በመላክ ወጣቶችን እንዲያረጋጉና እንዲያሳምኑ ማድረግ ነበር። የተሻለ የፖለቲካ አፈጻጸም አላቸው የተባሉ በሲቪል ሰርቪስና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ወደ ባህርዳር ተንቀሳቅሰው ወጣቱን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀርቷል።

የተለያዩ የፖሊስ ኮማንደሮችን ከአዲስ አበባ ወደ ከተማዋ በማስገባት የስነ ልቦና ጫና መፍጠር ይህ ካልተሳካም የፌደራልና የክልሉ ፖሊሶችን በማንቀሳቀስ ፍርሃት በመፍጠር ወጣቱ ወደ አደባባይ እንዳይወጣ የተቀየሰው ስትራቴጂ ውጤት አልባ ሆኗል።

በተቃውሞው ማግስት ብአዴን ነባር አመራሮችን በአስቸኳይ ወደ ባህርዳር በመጥራት ዝግ ስብሰባ እያካሄደ ነው። ንቅናቄው እስካሁን ድረስ በሰልፉ ዙሪያ ወይም በአቶ አለምነው ንግግር ላይ የአቋም መግለጫ አላወጣም።

በባህርዳር የተካሄደው ሰልፍ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም ዘጋቢያችን ገልጻለች። አንዳንድ የብአዴን አባላት ሳይቀሩ ህዝቡ ባሳየው ተሳትፎ ከሁሉም በላይ ስለነጻነቱ፣ ስለ ኢኮኖሚውና ፍትህ አንግቦ የተነሳው ተቃውሞ እንዳስደሰታቸው ለዘጋቢያችን ገልጸውላታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አለምነው መኮንን የአቶ መለስ ዜናዊ ጭፍን አምላኪ ተደርገው እንደሚቆጠሩ ጓዶቻቸው ለኢሳት ተናግረዋል። አቶ አለምነው በባህርዳሩ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብቸኛ የርእዮት አለም ሰው መለስ ዜናዊ እንደነበርና ሌላው ሁሉ ተከታይ መሆኑን መናገራቸው የአቶ መለስ ፍልስፍና አራማጅ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። ” ቢቀዳ ቢጨለጥ አንድ የርእዮት አለም ሰው የነበረው መለስ ዜናዊ ነው” የሚሉት አቶ አለምነው፣ ሌላው ሁሉ ተከታይ” ነው በማለት የኢህአዴግን አባላት ሳይቀር ከላይ እስከታች ተከታዮች አድርገው ፈርጀዋቸዋል። ” ሱፍ ለብሶ በመሄድ” አይደለም ሲሉም በአገሪቱ ባሉ ምሁራንና በኢህአዴግ መሪዎች ላይ ሳይቀር ተሳልቀውባቸዋል።

ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ አዳዲስ ሃሳቦች የሚያመነጭ የርእዮት አለም ሰው ሰው የለውም ማለት ነው ሲሉ በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አንዳንድ የብአዴን አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከ 6 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባላት መካከል እንዴት አንድ ሰው እንኳ አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ብቃት የሌለው ይጥፋ በማለት አባላቱ ጠይቀዋል።

አቶ አለምነው አማራውን በተመለከተ የተናገሩት አቶ መለስ በተደጋገሚ ሲጽፉትና ሲናገሩት የነበረውን ያሉት አንዳንድ አመራሮች፣ ብአዴን በአማራው ስም የተደራጀ የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ ድርጅት ነው እየተባለ የሚነገረው እውነት በመሆኑ፣ ድርጅቱን ከህወሃት ፈልቅቆ ለማውጣት የውስጥ ትግል እየተካሄደ መሆኑንም አክለዋል።