“የባህርዳር ህዝብ አንግቦ የተነሳው በአገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የለውጥ ጥያቄ ነው” ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

የካቲት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የ28 አመቱ ሙላት የመሸንቲ ነዋሪ ነው፤ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተገኘሁት በአገዛዙ ተማርሬ ነው ይላል። ለምን ተማረርክ በማለት ዘጋቢያችን ላቀረበችለት ጥያቄ፣ “ምን የማያስመርር ነገር አለ፣ ሁሉም ነገር እየተበላሸ እንጅ እየተሻሻለ ሲሄድ አታይም፣ ይህም አልበቃ ብሎ ይዘልፉናል” በማለት በሰልፉ ላይ የተገኘበትን ምክንያት ገልጿል።

የባህርዳር ነዋሪዎች አንድነትና መኢአድ በጋራ በጠሩት ሰልፍ ላይ በነቂስ ወጥተዋል። “ህዝብን እያዋረዱ መግዛት አይቻልም፣ብአዴን ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ የመግዛት የሞራል ልእልና የለውም፣ ህዝብ ከእርስት ማፈናቀል ይቁም፣ ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል፣ ነጻነት የሌላት አገር ጨለማ ናት፣ ገበሬው በገዛ መሬቱ ስደተኛ አይሆንም” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተስምተዋል።

“ዛሬ ታላቅ ደስታ ተስምቶኛል፣ የአመታት ህመሜ ተፈውሷል” ሲል የተናገረው የቀበሌ 7ቱ ነዋሪ ማሙሽ፣ ሰልፍ እንደሚደረግ ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ ሲቀሰቅስ መቆየቱን ተናግሯል።

አቶ አለምነው መኮንን የአማራን ህዝብ መዝለፋቸውን ተከትሎ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የባህርዳር ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ባንዲራ፣ አንዳንዶችም ጥንታዊት ኢትዮጵያን በሚወክሉ የጀግንነት ማጌጫዎች ተውበው በአደባባይ ተይተዋል።

ይሄ ህዝብ ማስፈራሪያዎችን ሁሉ ጥሶ፣ የቀን አበል ሳይሰጠው ለነጻነቱ በፍላጎቱ የወጣ ህዝብ ነው ያለው መኮንን፣ ገዢው ፓርቲ ይህንን ሰልፍ ለማውገዝ ሌላ ሰልፍ ሊያዘጋጅ እንደሚችል ይናገራል።

“ወጣቱ ፣ ሽማግሌው ሴቱ ወንዱ ተነስቷል” የሚለው ሌላው ነዋሪ፣ ህዝቡ ለነጻነቱ ሲጠይቅ መዋሉን ገልጿል።

“ከሰለፉ ማግስት ባህርዳር እንዴት ናት?’ በማለት ሲጠየቅም፣ ” ህዝቡ ደስ ብሎት በእየቤቱ እየተወያየ ነው” ብሎአል ። ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በሰልፉ ላይ የታየውን ዲሲፒሊን አድንቋል።

የአቶ አለምነው መኮንን ጉዳይ የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ እንደ መነሻ ሆነ እንጅ ዋናው ጥያቄ የዲሞክራሲ፣ የነጻነት እና የኢኮኖሚ መሆኑን ገልጿል። “ኢህአዴግ እንደተናካሽ ውሻ በድንጋጤ ያገኘውን ሁሉ ለመንከስ ቢሞክርም፣ ትግሉ ግን ወደ ሁዋላ የሚቀለበስ አይመስለኝም ሲል አስተያየቱን አክሏል።