የካቲት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈዉ ቅዳሜ የካቲት 15፣ 2006 ዓም በ ኒዉዚላንድ አገር በኦክላንድ ከተማ ተዘጋጅቶ የነበረዉ የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
በሂደቱ በርካታ ችግሮች ተጋርጠውበት የነበረ ቢሆንም፣ ለአገራቸዉ ነፃ መዉጣትና ኢሳትን አሁን ካለበት እጥፍ አድጎ ማየት በሚፈልጉ ቀናኢ ኢትዮጵያዉያን ጥረት የገንዘብ ማሰባሰቡ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስተባባሪዎች ገልጸዋል።
በርካታ ኢትዮጵያን የነበረዉን መሰናክል በማለፍ በቦታዉ የተገኙ ሲሆን ከ ዌሊንግተንና ክራይሰት ቸርች የመጡ የ ኢሳት ደጋፊዎችም እንዲሁ የዝግጅቱ ተካፋይ ለመሆን በሺ ኪሎ ሜትር ተጉዘዉ ተገኝተዋል። ቤተሰብ ለመጠየቅ ከአዉስትራሊያና አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያዉያኖችም በዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ዝነኛዉ አርበኛ አርቲስት ሻምበል በላይነህ ከ አገራዊ እና ባሕላዊ ዘፈኖቹ ጋር በመቅረብ ዝግጅቱን በልዩ ሁኔታ አድምቆታል።
ቀደምት አባት አርበኞችን ባቀፈዉ የኢትዮጵያ ካርታ ምስል በርካቶች በኢትዮጵያ ጀግኖች ስም ተጫርተው፣ጨረታውን አቶ አረፈ አይኔ የተባሉ ሰው አሸንፈዋል። በዚህ የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት ላይ የኒዉዚላንድ የኢሳት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ ጊዜያዊ ሰብሳቢ አቶ መላኩ በገንዘብ አሰባሰቡ ላይና አዲስ በተከፈተዉ የ አዉስትራሊያ ባንክ እንዴት ገንዘቡን ማስገባት እንደሚቻልና ቋሚ አባል መሆን እንደሚገባ ዘርዝረዉ በማስረዳት ኢሳትን በቋሚነት መርዳት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አንዱአለም ሃይለማርያም ከኒውዚላንድ ዘግቧል።