በሱዳን ጎረምሶች የተደፈረችው ኢትዮጵያዊት በአንድ ወር ተቀጣች።

የካቲት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በድንጋይ ተወግራ ልትገደል ትችላለች በማለት የእንግሊዙ ዘ ጋርድያንና ኢንዲፕንደት የተባሉት ጋዜጦች ቢዘግቡም፣ የሱዳን ፍርድ ቤት ወጣቱዋን በአንድ ወር ብቻ ቀጥቷታል። ይሁን እንጅ ነፍሰጡር በመሆኗ ከእስር ነጻ ሆና ወደ አገሩዋ እንድትመለስ እና 4 ሺ የሱዳን ፓውንድ እንድትከፍል መወሰኑዋን ቢቢሲ ዘገበ።

ከልጅቷ ጋር ጾታዊ ግንኙነት የፈጸሙት 3ቱ ወጣቶች 100 ጊዜ እንዲገረፉ፣ ፊልሙን በመቅረጽ ያሰራጩት ደግሞ 40 እንዲገረፉ ተወስኖባቸዋል። ወጣቱዋ በድንጋይ ተወግራ ከመሞት የዳነቸው ከባላዩዋ ጋር የተፋታች መሆኑዋን በመስመስከሯ ነው። አይሳ የተባለው የሴቶች ኔትወርክ፣ በወጣቱዋ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተቃውሞአል። የተደፈሩ ሴቶች ለፖሊስ እንዳያመለክቱ የሚያደርግ ውሳኔ ነው ሲሉ ፍርደ ቤቱን ተቃውመዋል። የእንግሊዝ ጋዜጠኞች ለጉዳዩ ሰፊ ትኩረት በመስጠት ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው።