የካቲት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጉርሻ ክፍያው ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ እንዲሰጣቸው ተብሎ የጸደቀበትና የክፍያ ማዘዣው ከከተማ አስተዳድሩ ለሁሉም ወረዳዎችና ክ/ከተሞች በያዝነው ሳምንት እንደተላለፈላቸው ለማዎቅ ተችሎአል።
የጉርሻ ገንዘቡ ከ1 ሺ 700 እስከ 4 ሺ 000 ብር የሚደርስ ሲሆን አገልግሎቱም ለስልክ፣ ለቤት ኪራይ እና ለትራንስፖርት መደጎሚያ ታስቦ የሚሰጥ ነው። ክፍያው በፋይናንስ መክፍያ ሰነድ ወይም ፔሮል ላይ ሳይቀመጥ ከማንኛውም ታክስና ተቀናናሽ ውጭ ሆኖ በቀጥታ እጃቸው ላይ የሚደርስ ብር ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተቸገሩ ነው። በርካታ የመንግስት ሰራተኞች በተቀጠረበት መ/ቤት በትንሹ 3 ወራት እንኳ ሳይሰሩ የተሻለ የስራ መደብና ደመወዝ ፍለጋ በየማስታወቂያው ግድግዳ ላይ ቆመው እንደሚታዩና በስራ ማስታወቂያ ጋዜጦች ላይ ጊዜያቸውን እንደሚያጠፉ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጿል።
በክፍያ ችግር ምክንያት የመንግስት ሰራተኛው ስራውን ተረጋግቶ እየሰራ እንዳልሆነ የሚገልጸው ዘጋቢያችን፣ ከተለያዩ ቢሮዎች፣ ከ ክ/ከተማና የወረዳ ጽ/ቤቶች የሚፈልሱት የመንግስት ሰራተኞች ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው ብሎአል።
በመንግስት መ/ቤቶች ለቅጥር ማስፈጸሚያ ተብሎ በየጊዜው ለጋዜጣ ክፍያ የሚወጣው ወጭ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱንም የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ።
ከየመስሪያ ቤቱ በየጊዜው የሚፈልሰውን ሰራተኛ በስራው ላይ ለማቆየት አልያም ተረጋግ ስራውን እንዲሰራ ለማድረግ መንግስት ምንም አይነት የመፍትሄ እርምጃ ሲወስድ አለመታዩን እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ።
የአቅም ግንባታም ሆነ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊዎች የመንግስት ሰራተኛውን ለመደለል በየመድረኩ በቅርብ ቀናት ውስጥ ወጥ የሆነ የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት ይዘረጋል እያሉ ቃል ቢገቡም፣ ከቃል ባለፈ ምንም የተገኘ ነገር አለመኖሩን የመስተዳድሩ ሰራተኞች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ስር የሚገኙ የመንግስት መ/ቤቶች ና የልማት ድርጅቶች ወጥ የሆነ የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት ስለሌላቸው አነስተኛ ደሞዝ ከሚከፍለው መ/ቤት የተሻለ ክፍያ ወደ ሚከፍሉት በየጊዜው ይፈልሳሉ፡፡
በከተማ አስተዳድሩ ስር ከሚገኙት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች መካከል በአንጻራዊ መልኩ የተሻለ ክፍያ የሚከፍሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ እና የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ሲሆኑ ከሌሎች መ/ቤቶች ወደነዚህ መ/ቤቶች ለመቀጠር የሚሯጠው ሰራተኛ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
የመስተዳድሩ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ የሰራተኛ ፍልሰቱን ለመቋቋም ፣ ቀጥተኛ የስራ ልምድ ያለው እንዲቀጠር የሚል አዲስ መመሪያ ክለሳ አድርጎ አውጥቷል፡፡
የመንግስት ሰራተኞች እንደሚሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንዳንድ ቢሮዎች ባለፉት 6 ወራት ውስጥ የሰራተኛ ፍልሰቱን ለመቋቋም እና የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ያስችላል ያሉትን ለሰራተኛውና ለስራው የሚመጥን ደመወዝ አጥንተው የሰራተኛው ደመወዝ ክፍያ ደረጃው እንዲሻሻል ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ቢያቀርቡም በቂ ምላሽ አላገኙም።
የደመወዝ ጥናቱን ተከትሎ በተለይ ቀድመው አስጠንተው ያቀረቡ ቢሮዎች የደመወዝ ማስተካከያ ጥያቄው ቀርቦ እንደሚጸድቅ ለሰራተኞቻቸው ቃል ሲገቡ ቢቆዩም በከተማው ከንቲባ ውድቅ በመደረጉ የሰራተኞቻቸውን አይን ለማየት የሚያፍሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ሰራተኞች ይናገራሉ።
መንግስት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም በተለየ ከመንግስት ሰራተኛው ይልቅ ለፖለቲካ ካድሬዎቹ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚገኝ የሚናገሩት ምንጮች፣ ካድሬዎች ከከተማ ወጥተው የትኛውም ክልል ሲሄዱ እስከ 900 ብር የሚከፈል አልጋ ያለው ሆቴል ላይ እንዲያድሩ፣ እንዲሁም የፈለጋቸውን መኪና ለቤተሰብ ሳይቀር ከሙሉ የነዳጅ ወጪ ጋር እንደሚዘጋጅላቸው ሰራተኞችን ዋቢ በማድረግ ዘጋቢያችን ገልጿል።
የጉርሻ ገንዘቡ የተፈቀደላቸው ዋና ዋና ሹሞች የገዢው ፓርቲ አባላት ናቸው።