የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ አሸባሪ ካላቸው ግንቦት ሰባት እና ሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ የአዲስ አበባና አማራ ክልል ወጣቶች ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት እየተጋዙ መሆኑን የአይን እማኞች ተናገሩ፡፡
ኢህአዴግ በጀመረው አዲስ አሰሳ በሀገሪቱ አንድንድ ቦታዎች ኢንተርኔትን ጨምሮ ስልክ እንዳይሰራ የተደረገ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም የመከላከያ ሀይል ተበትኗል፡፡ የዚህን ዜና ዝርዝር በሌላ ጊዜ ይዘን እንቀርባለን። በሌላ ዜና ደግሞ ብአዴን ከፍተኛ የሞራል ውድቀት የደረሰበት መሆኑን ምንጮች ገለጹ።
የብአዴን የጽፈት ቤት ሃላፊ እና የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አለመነው መኮንን የሚመሩት ህዝብ ጸያፍ ስድብ መሳደባቸውን ተከትሎ ብአዴን የሞራል ውድቀት እንደደረሰበት ከክልሉ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የክልሉ ህዝብ ያሳየው ቁጣና በብአዴን የንግድ ድርጅቶች ላይ የጣለው ማእቀብ ያሰጋቸው አቶ በረከት ስምኦን ወደ ባህርዳር በማቅናት ፣ የደረሰውን ኪሳራ ለመቋቋም ያስችላሉ የሚሉዋቸውን አማራጮች ሁሉ ለመጠቀም ከሌሎች አመራሮች ጋር እየመከሩ ናቸው።
የብአዴን አመራሮች ባደረጉት የመጀመሪያ ግምገማ “የአማራ ህዝብ ፊት ለፊት የምንናገረውና ከጀርባ የምንናገረው ነገር የተለያየ ነው” ብሎ እንዲያስብና እምነቱን እንዳይጥልብን አድርጓል” ብለዋል። ብአዴን በመጪው ምርጫ ላይ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ሊደርስበት እንደሚችልም በግምገማው ወቅት ተነስቷል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በኢሳት የቀረበው የአቶ አለምነው ድምጽ አይደለም ብለው ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል። ፕሬዚዳንቱ በባህርዳር ስብሰባ መካሄዱንና ድምጹም በጊዜው የተቀረጸ መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ ያመኑ ሲሆን፣ መክትላቸው የተናገሩትን በቀጥታ ከማስተባበል ይልቅ አቶ አላምነው ለአማራው ህዝብ ስላላቸው ፍቅር መግለጽን መርጠዋል።
አቶ አለምነው እራሳቸው ቀርበው ለምን መግለጫ እንዲሰጡ እንዳልተፈለገ ግልጽ አይደለም። የክልሉ ህዝብ የብአዴን ንብረት የሆነውን ዳሸን ቢራን እንዳይጠጣ የሚደረገው ቅስቀሳ አግባብ አይደለም ሲሉ አቶ ገዱ ተናግረዋል።
ድርጊቱን ያወገዙት አንድነትና መኢአድ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል። ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ” ህዝብ ያዋረዱ አመራሮች በተገቢው ፍጥነት ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ የተቃውሞ ሰልፉ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ ከጣቱ በሶስት ሰአት ከቀበሌ 12 ( ግሽ አባይ ተነስቶ)፣ በክልሉ መስተዳድር ጽ/ቤት ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ ያበቃል። የባህርዳር እና አካባቢዋ ህዝብ በስፍራው ተገኝቶ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በህዝቡ ላይ ያወረዱትን ዘለፋ እንዲያወግዝ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።