የካቲት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ተወላጆች ላይ በጅምላ ፀያፍ ስድብ የሰነዘሩት የብአዴኑ አመራር እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የ አቶ ኣለምነው መኮነን መኖሪያ ቤት በድንጋይ መደብደቡን ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ የዘገበ ሲሆን፣ ዜናውን ተከትሎ ኢሳት ባደረገው ማጣራት የባለስልጣኑ መኖሪያ ቤት በ11 ፖሊሶች ሌትና ቀን እየተጠበቀ ነው።
አቶ አለምነው የአማራው ህዝብ የትምክህት ለሃጩን በማራገፍ ከሌላው ህዝብ ጋር ለመኖር መልመድ አለበት በማለት የተናገሩት በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ወጣቶች በሞባይል ስልካቸው ንግግሩን በመቅረጽ እያሰራጩት ነው።
አቶ አለምነው እስካሁን በይፋ ህዝቡን ይቅርታ አልጠየቁም ወይም በኢሳት የቀረበውን መረጃ ለማስተባበል አልሞከሩም። ኢሳት ም/ል ፕሬዚዳንቱ የተናገራቸው በርካታ ንግግሮች የደረሱት ሲሆን እንዳስፈላጊነቱ ወደ ፊት ለህዝብ ይፋ ያደርጋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የአቶ ተመስገን ዘውዴን የህይወት ታሪክ የሚዳስሰውን መጽሐፍ በማሳተሙ የስም ማጥፋት ክስ የተመሰረተበት የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ደራሲ ዳንኤል ተፈራ ዛሬ በድጋሚ ማዕከላዊ ተጠርቶ ለሰኣታት መታሰሩ ተዘግቧል።
ፍኖተ ነፃነት እንደዘገበው አቶ ዳንኤል ከሰዓታት እስር በሁዋላ በድጋሚ የተከሳሽነት ቃሉን ሰጥቶ መኪና ሊብሬ በዋስትና አስይዞ ከእስር ተፈቷል፡ የፓርቲው ሌለኛው አመራር አቶ አሥራት ጣሴ ፦”አኬልዳማ ድራማን አስመልክተን መንግስትን የከሰስነው ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ፍትህ እናገኛለን ብለን ሳይሆን ለታሪክ እንዲመዘገብ ነው” የሚል አስተያታቸውን በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ በመፃፋቸው ታስረው ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የተጋዙት ከቀናት በፊት ነው።
ቀደም ሲልም የፓርቲው አመራር የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌና አቶ ናንትናኤል መኮንን ሀሳባቸውን በመግለፃቸው ሳቢያ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በእስር እንደሚገኙ ይታወቃል።