የዩጋንዳ ጦር ደቡብ ሱዳንን ለቆ እንዲወጣ አቶ ሃይለማርያም አስጠነቀቁ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚ/ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የዩጋንዳ ጦር በሂደት ለቆ ካልወጣ አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ሁሉም ሃይሎች የራሳቸው የሆነ ፍላጎት አላቸው ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም ይመጣ ዘንድ የዩጋንዳ ጦር ጁባን ለቆ መውጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል ።

አቶ ሃይለማርያም የገለጹት አቋም የደቡብ ሱዳንን መንግስት የሚያስከፋ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን ለተቀዋሚዎች መልካም ዜና ነውተብሏል። የሳልቫኪር መንግስት፣” ሰላማችንን ለማስጠበቅ  የፈለግነውን ሃይል የመጋበዝ መብት አለን” የሚል አቋም ይዟል።

ዩጋንዳ ለአቶ ሃይለማርያም ማስጠንቀቂያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። የዩጋንዳ መንግስት በአቋሙ ከጸና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የደቡብ ሱዳን ጎረቤት አገሮች የሚወስዱት አቋም ግልጽ አይደለም።

የዩጋንዳ ጦር ፕሬዚዳንት ሳለቫኪር በተቃዋሚዎች ላይ ድል እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ዘገባዎች ያመለክታሉ።