በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግሩ እንደተባባሰ ነው

የካቲት  ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በከተማው ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ፣ የግል ባለንብረቶችና ባለታክሲዎች በመላ አገሪቱ የጠፋውን ነዳጅ ተከትሎ ነዳጅ ለማግኘት ላይ ታች እየተንከራተቱ ሲሆን፣  የነዳጅ መጥፋቱን  ተከትሎ የትራንስፖርት ታሪፊም  ጨምሯል። ዘጋቢያችን እንዳለው ዛሬ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ 0.25 ሳንቲም ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል ተገዷል፡

ነዳጅ ማደያዎችን ተዘዋውሮ የተመለከተው ዘጋቢያችን፣ በከተማው የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ናፍጣም ሆነ ቤንዚን በማጠራቀሚያቸው  ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንደሌለ እንደተገለጸለት ይህንን ተከትሎ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ እንደጨመረ ገልጿል።

ከመኪና አገልግሎት ውጭ ነዳጅ እንዳትሸጡ ተብለው የታዘዙት የማደያ ባለቤቶች፣  ለመኪኖቹ በወረፋ ለማከፋፈል በሚያደርጉት ሙከራ፣ ነዳጅ መሸጫ ቦታዎች በመኪኖች ሰልፍ ለመጨናነቅ

የማዲያ ሽያጭ ሰራተኞች ሰልፉን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በአካባቢ ፖሊስ እየታገዙ በማስተናገድም ላይ ናቸው፡፡

የከተማዋ ትራንስፖርት መስመሮችና መንገዶች በተለያያ አቅጣጫ ከቁጥጥር ወጭ በሆነ ሁኔታ እየተቆፈሩ በመሆኑ ብዙ መንገዶች በግንባታ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት መስመር መጨናነቅ አጋጥሟቸዋል።

የትራንስፖርት እጥረቱ በመንግስት ስራም ላይ  አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የሚገልጸው ዘጋቢያችን፣ የመንግስት ሰራተኛው ከ4 ሰዓት በኋላ ስራ ለመግባት ተገዷል።

መንግስት ለነዳጅ መጥፋቱ የሰጠው ምክንያት የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችን የሚያሳምን አልሆነም። የንግድ ሚኒስትሩ የነዳጅ አቅርቦት እትረት የተከሰተው አንዳንድ ነጋዴዎች በትርፍ ለመሸጥ በመፈለጋቸውና ኦይል ሊቢያ የተወሰኑ የነዳጅ መኪና ማመላለሻ ቦቴዎችን ለሌላ ድርጅት በማስተላለፉ ነው የሚል መልስ መስጠታቸው ይታወቃል።