በአዲስ አበባ በሌሊት የሚጻፉ የተቃውሞ ጽሁፎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የካቲት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከታህሳስ ወር 2006 ዓም ጀምሮ በመዲናዋ  ሌሊት የሚጻፉ  የተቃውሞ ጽሁፎችን ማየት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ትናንት ሌሊት በአስኮ መስመር ጀኔራል ዊንጌት ከሚገኘው አደባባይ ጀምሮ አወሊያ፣ካኦጄጄ፣ አስኮ የሚወስደውን ዋና መንገዱን በመሃል በሚከፍለው እስከ 2.5 ሜትር ቁመት ባለው ግድግዳ ላይ የሙስሊሙን የመብት ጥያቄና የትግል ቀጣይነት የሚያንፀባርቁ ጽሁፎች በተለያዩ ቀለማት ተጽፈው ዛሬ ህዝብ ሲያነባቸው ታይቷል።

በአዲስ አበባ ጦር ሀይሎች፣ ወይራ ሠፈር ፣ አዉጉሥታ፣ቤቴል እና ሌሎችም አከባቢዎች ተመሳሳይ መልእክቶችን ያዘሉ ጽሁፎች ተለጥፈው ማደራቸውን ለማወቅ ተችሎአል፡፡

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጽሁፎችን በተመሳሳይ ቀለም ለማጥፋት ሙከራ እንደሚያደርጉ አልሆን ሲልም ስሚንቶ በመለጠፍ ለማጥፋት እንደሚሞክሩ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።