ጥር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኦክላንድ የምርምር ተቋም ውሳኔውን ታሪካዊ ብሎታል።
በኮንግረሱ የጸደቀው ኦምኒበስ አፕሮፕሬየሽንስ ቢል እየተባለ የሚጠራው ህግ (Omnibus Appropriations Bill) አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ ዜጎችን ለማፈናቀል እንደማይውል፣ ይህንንም ተከትሎ ሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ያረጋግጣል።
በኦሞ ሸለቆና በጋምቤላ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ነዋሪዎችን በማፈናቀል በሚደረገው ልማት ላይ የአሜሪካ እርዳታ ጥቅም ላይ እንዳይውል ህጉ ይከለክላል። የአሜሪካ እርዳታም የአካባቢውን ነዋሪዎች ለመጥቀም ብቻ እንዲውል አፈጻጸሙም ከህዝቡ ጋር በመመካከር ብቻ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል።
ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ የሚያደርጉ አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማትም፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ማንኛውም ድጋፍ ዜጎችን የማያፈናቅል እና ሰብአዊ መብቶችን የማይጥስ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ሲል ኮንግረሱ ውሳኔ አሳልፏል።
የኦክላንድ ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አኑራዳሃ ሚታል ” ውሳኔው የአሜሪካ እርዳታ እስከ ዛሬ ሲሰጥበት የነበረውን የተሳሳተ መንገድ የሚያስተካከል በመሆኑ ተቀብለነዋል።” ብለዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ” የአሜሪካ ኮንግረስ የወሰደው እርምጃ ከእንግዲህ በልማት ስም የሚደረግ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተቀባይነት እንደሌለው ለኢትዮጵያ መንግስትና ለአሜሪካ አስተዳደር ግልጽ መልእክት ያስተላለፈ ታሪካዊ” ውሳኔ ነው ብለዋል።
ከእንግዲህ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ( ዩኤስ አይ ዲ) እንዲሁም የአለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንደገና መፈተሽ ይኖርባቸዋል ።
የኦክላንድ ተቋም የፖሊሲ ዳይሬክተር ፍሬድሪክ ማውሲዩ እንዳሉት ውሳኔው የአለማቀፍ ድጋፍ ሲሹ ለነበሩት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው ።
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።