ጥር ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 16፣ 2006 ዓም ባስቻለው ችሎት በእነ አቶ ደፋሩ ዶሬ መዝገብ የተከሰሱ 13 ሰዎች በሙሉ በ2 አመት ከ9 ወራት እስር እንዲቀጡ ወስኗል። በውሳኔው መዝገብ ላይ እንደተመለከተው እስረኞቹ የተፈረደባቸው “ እኛ ወይም ቁጫ የጋሞ ብሄረሰብ አይደለንም በሚል ህዝብን አነሳስታችሁዋል፣ ህገወጥ ስብሰባ አድርጋችሁዋል፣ እንዲሁም የጸረ- ህዝብ አቋም አራምዳችሁዋል” በሚል ነው።
እነዚህ እስረኞቹ ቀደም ብሎ በቁጫ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት በዋስትና እንዲወጡ ከተደረገ በሁዋላ እንደገና ተመልሰው እንዲታሰሩ ተደርጎ ያለፉትን 6 ወራት በእስር ቤት አሳልፈዋል። ፍርዱ የተሰጣቸውም እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ነው።
እስረኞቹ በአካባቢው ህዝብ በሽማግሌነት ተመርጠው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ በመሄድ አቤት ብለው ነበር። በቁጫ አሁንም እስር እና ሰዎችን ማሰደድ እንደቀጠለ ሲሆን፣ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጸረ ሰላም ሃይሎች እጅ አለበት በሚል በአካባቢው የጸጥታ ሃይሎች እንዲሰማሩ አድርጓል። ከቁጫ የማንነት ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከ200 እስከ 400 የሚደርሱ ሰዎች ታስረዋል።