ጥር ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጋዜጣው አዘጋጆች በማህበራዊ ድረገጾች ላይ በለቀቁት ዜና “በሰንደቅ ጋዜጣ ቁጥር 434 ታህሳስ 23 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው “ጉዲፈቻ፤ በኢ-ሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ የኪራይ ሰብሳቢዎች ዋሻ ተንኳኳ” በሚል ርዕስ በገጽ 5 በፖለቲካ ዓምድ ላይ በሰፈረው ጽሁፍ መነሻነት የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ እና በም/ዋና አዘጋጁ ፋኑኤል ክንፉ ላይ የክስ አቤቱታ መስርቷል” ብለዋል።
ሐሙስ ጥር 15 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ክፍል የተሰማው የክስ አቤቱታ ” ሰንደቅ ጋዜጣ የአገር ገጽታን በማበላሸት፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋምን ገጽታ በማበላሸት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን እና የፖሊስ ተቋማትን ታማኝነት እንዳይኖረቸው በዘገባቸው አድርገዋል” የሚል እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ በፌደራል ፖሊስ (በቀድሞ ማዕከላዊ ፖሊስ ትናንት ጠዋት) በመቅረብ ተቋሙ በቀረበበት የክስ አቤቱታ በአምስት ሺህ ብር ዋስ መለቀቃቸውን ዜናው ይጠቅሳል፡፡ ሚኒሰቴሩ ባቀረበው ክስ አቤቱታ ተጠያቂ ያደረጉት ዋና እና ምክትል ዋና አዘጋጆቹን ነው ፡፡ አዘጋጆቹ የሰጡት መልስ በዜናው ውስጥ አልተካተተም። ሰንደቅ ጋዜጣ በገዢው ፓርቲ ከሚደጎሙ ጋዜጦች መካከል አንዱ ነው በሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል፣ ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋዜጣው አዘጋጆች በተለያዩ ክሶች ፖሊስ ጣቢያ እየተመላለሱ ይገኛሉ።