ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በቦረናና በቡርጂ ማህበረሰብ አባላት መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ከ4 ሺ በላይ ነዋሪዎችም ቀያቸውን ጥለው ከተፈናቀሉ በሁዋላ፣ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ቦታው በመሄድ ለማረጋጋት ሙከራ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩ እንደገና በመቀስቀሱ ከ1ሺ በላይ የቡርጂ ጎሳ አባላት አካባቢውን ለቀው ወደ ደቡብ ክልል አምርተዋል።
ከሜጋ ከተማ ወደ 12 ኪሎሜትሮች ርቀው ከሚገኙት ጎዳቤሮ፣ ባታንጋላዶ እና ኦላ ጫፋ ወደ ሚባሉት ቀበሌዎች ይኖሩ የነበሩ ቡርጂዎች መሬቱ የእናንት አይደለም ተብለው እንዲወጡ መደረጋቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።
በቅርቡ የተነሳው ግጭት መነሻ አንድ የቦረና ሰው ተገድሎ መገኘቱ ሲሆን፣ የልዩ ዞኑ ምክትል አዛዥ የሆኑት አቶ ሊባን አሬሮ እጅ እንዳለበትም ይገልጻሉ። አቶ ሊባን የተባሉት ባለስልጣን በምን ምክንያት እንደሞተ ያልታወቀውን ሰው ቡርጅዎች ገድለውታል ብለው የአካባቢውን ሰው ቀስቅሰው ወደ ግጭት እንዲያመራ አድርገውታል በማለት ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸው ነበር።
በቅርቡ ኬንያ ውስጥ በገብራና በቦረናዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ቡርጅዎች ከገብራዎች ጎን ቆመው ቦረናዎችን ወግተዋል በሚል በሁለቱ ህዝቦች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ማድረጉን ገለልለተኛ ወገኖች ይናገራሉ። ባለፉት 3 ቀናት የታየውን መፈናቀል በተመለከተ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አካባቢው ሰው እንደተናገሩት፣ ቡርጂዎች ከብቶቻቸውን እየተቀሙ ቦረናን ለቀው ወደ ደቡብ ክልል ተሰደዋል። እስከ ትናንት ድረስ ከ1 ሺ 200 በላይ ቡርጂዎች መሰደዳቸውን ገልጸዋል።