የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር እስካሁን ውጤት አላሳየም

ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመንግስት እና በአማጽያን መካከል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ድርድር እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ሁለቱም ሀይሎች በሚያቀርቡዋቸው ቅድመ ሁኔታዎች እስካሁን ውጤት አለመገኘቱ ታወቀ።

አማጽያኑ የታሰሩት ባልደረቦቻቸው እንዲፈቱ፣ የዩጋንዳ ጦር አገሪቱን ለቆ እንዲወጣና የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያበቃ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡ ሲሆን፣ በመንግስት በኩል ደግሞ በአማጽያኑ የቀረቡትን በተለይም እስረኞችን መፍታት የሚለውን ቅድመ ሁኔታ አልተቀበለውም። ነገሮች እየባሱ ሄደው አንደኛው ሌላውን የውጭ መንግስታት ቅጠረኛ በማለት እየጠሩ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንግስት ሃይሎችና ተቃዋሚዎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን የድርጅቱ ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሃላፊ የሆኑት ኢቫን ስሞኖቪች ገልጸዋል።

ቤንቲዩ እና ጎር የተባሉት ከተሞች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የገለጹት ሃለፊው በርካታ ስደተኞች በተመድ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ መጠለላቸውን ገልጸዋል። ከ80 ሺ ያላነሱ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ  ኢትዮጵያና ሌሎች ጎረቤት አገሮች መሰደዳቸውንም ዘገባዎች ያመለክታሉ ። ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኖችን በተመለከተ ስለደረሰውና ስለሚደርሰው ችግር እስካሁን ድረስ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም።