ለውዝግቡ መነሻ የሆውን እና የኢትዮጵያውያንን ስሜት የሚጎዳውን ጽሁፍ ያተመው ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንድያ ጋዜጣ ዘገባውን እንዲያርም፣የኢትዮጵያ ኤምባሲም ማስተባበያ እንዲሰጥ በህንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጠይቀዋል።
በህንድ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ያስቆጣው ዘገባ፣ በዘ ታይምስ ኦፍ ኢንድያ ኦክቶበር 20/2011 የወጣው እትም ነው።
ለዘገባው መነሻ የሆነው ከኦክቶበር 15 እስከ 21/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር የባህል ቡድን በኢንዲያን ኢንተርናሽናል ሴንተር ያሳየው የሙዚቃ ትርኢት ነው፤
ይህንን የሙዚቃ ትርዒት በተመለከተ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ኦክቶበር 20/2011 የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ያሳዩትን ትርዒት በተመለከተ ባቀረበው ዘገባ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ባህል ቡድን የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰብ ጭፈራዎችን አቅርበዋል፤ አርቲስቶቹ ያቀረቧቸውን ጨዋታዎች የአማራ፣የትግሬ፣የአገው፣የአደሬ፣የኩሎ እና ከፊቾ እንዲሁም የ 6 ኦሮሞ ጎሳዎች ጭፈራ እንደሆነም ተመልክቷል፤ ጋዜጣው ብሔረሰቦቹን ሲጠቅስ በተለይ አንዱ ብሔረሰብ ላይ የተጠቀመበት ቋንቋ ቁጣ መቀስቀሱ እና ውዝግብ ማስከተሉን ነው መረዳት የተቻለው።
ዘገባውን ያነበቡ በህንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ዘገባው የተሳሳተ ቃላት መጠቀሙን በመግለጽ እርማት እንዲያወጣ ሲጠይቁ፣ድረገጹ የመረጃው ምንጭ ኤምባሲው ስለሆነ እነሱ ካልጠየቀኝ አላስተባብልም አለ፤ተማሪዎቹ ወደ ኤምባሲው በመሄድ የሚመለከተውን ሰው ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ የተሳካው ሰኞ እለት መሆኑን ከህንድ ዴሊ የደረሰን መረጃ ያስረዳል፤ ሰኞ ኦክቶበር 24/2011 ተማሪዎቹን ያነጋገሩት አቶ መታሰቢያ ታደሰ የተባሉ የኤምባሲው ባለስልጣን ናቸው፤ ሰውየው በተማሪዎቹ ስለዘገባው ሲጠየቁ በቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በቅርብ ስለመስራታቸው ተናገሩ፤ ለ6 ዓመታት የአቶ መለስ የፕሮቶኮል ሹም እንደነበሩ በማስታወስ ወደ ጉዳዩ ተመለሱ፤ የተዛባው ቃል ለታይምስ ኦፍ ኢንዲያ የሰጣችሁት ተማሪዎች መሆናችሁን ደርሰንበታል በማለት ተማሪዎቹን አስጠነቀቁ፤በዚህም ሳይማሙ በመወነጃጀል ተለያይተዋል፤ኤምባሲው ጉዳዩን እንዲተዉትም ተማሪዎቹን እንዳስጠነቀቃቸው የደረሰን ዜና ያብራራል።
ለ ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ትርዒቱን በተመለከተ መረጃውን የሰጠው ኤምባሲው እንደሆነ በዘገባው አስፍሯል፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአራት እንደሚከፈል የዘረዘሩት የኤምባሲው ከፍተኛ ባለስልጣን መሆናቸውም
በዜናው ተመልክቷል፤ ትርዒቱን ያቀረበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር በ1940 ዎቹ እንደተመሰረተ እና ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ቲያትር ቤት ይባል እንደነበር የዘረዘረው የህንዱ ሚዲያ ውዝግብ ቀስቃሹን ጉዳይ ለምን ሳይደርስበት እንደቀረ የታወቀ ነገር የለም።