የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ ጸደቀ

ጥር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ከተሞች ሥር የሰደደውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳል የተባለ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ በፓርላማ ጸደቀ፡፡

አዋጁ በተበታተነና በልማዊ መንገድ ሲካሄድ የነበረውን የመሬት ባለቤትነት ይዞታ አሰራርን በዘመናዊ መልኩ እንዲካሄድ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው ተብሎአል፡፡

የመሬት ይዞታ መብት ይፋዊ ምዝገባ ከመነሻው መሰረቱ የከተማ ቁራሽ መሬት ማድረጉን ከከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ የሚያብራራ ሲሆን ምዝገባው በከተማ ያለውን የመሬት አስተዳደር ግልጽ በማድረግ፣ ግልጽ መረጃ እንዲኖር እንደሚደርግ ተመልክቶአል፡፡

አዋጁ የግል ባለሃብቱን በመሬት የመጠቀም መብት በማስጠበቅ አመኔታ ያተረፈ የመሬትና መሬት ነክ ስርኣት እንዲሰፍን እንደሚያደርግ የተመለከተ ሲሆን የግል ባለሃብቱ በይዞታ ባለቤትነት ላይ እምነት ሲፈጥር በማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ፣በሪልስቴት፣በኮንስትራክሽን፣በመሰረተ ልማትና በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ የሚሰማራውን ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በገንዘብ ተቋማት ደረጃ በሚያሳድረው የመረጃ አስተማማኝነት በጎ ተጽዕኖ ምክንያት ዜጎች የቆጠቡትን ሃብት በአበዳሪ ተቋማት አማካኝነት ወደኢኮኖሚው እንዲያፈሱ ያነሳሳል ሲል የሚኒስቴሩ መረጃ ይተነትናል፡፡

አዋጁ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን ደንብና መመሪያ ተላልፎ ይዞታን የማረጋገጥ ስራ ያከናወነ ሹም ወይም ሰራተኛ ከ5 አስከ 15 ዓመት እስራትና ከብር 40 ሺህ እስከ ብር 200 ሺህ እንደሚቀጣ፣ የመሬት ይዞታን ከመዘገበ ደግሞ ከ5 አስከ 10 ኣመት እስራትና ከብር 30 ሺህ እስከ150 ሺህ ብር መቀጮ እንደሚጣልበት ደንግጓል፡፡

በምዝገባው ስራ የማይተባበሩ ዜጎች ከብር 1ሺህ እስከ 3 ሺህ ቀላል መቀጮ እንደሚጣልባቸው ፣የተጭበረበረ ሰነድ የሚያቀርቡ ወገኖች ደግሞ ከ5 እስከ 15 ዓመት እስራትና ከብር 40ሺህ እስከ 200ሺህ ብር መቀጮ እንደሚጣልባቸው ደንግጓል፡፡

አዋጁ ይጽደቅ እንጂ መዝጋቢ አካላት እስኪቋቋሙ ድረስ ላልታወቀ ጊዜ ስራ ላይ እንደማይውል
በአዋጁ ላይ ተመልክቷል፡፡