ታህሳስ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተለይ ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውና በታችኛው አመራር ጭምር ሊፈቱ የሚገቡ ጉዳዮች ተጠያቂነትን ከመፍራት አኳያ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሩ የመግፋት ጉዳይ በተደጋጋሚ መከሰቱ አሳሳቢ መሆኑ ሰሞኑን በተደረገው ግምገማ ላይ ቀርቧል፡፡
አስተዳደሩ የ2006 የመጀመሪው ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም በገመገመበት መድረክ ላይ ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል ስራዎችን ወደላኛው አካል የመግፋት ጉዳይ በበጀቱ ኣመቱ አሳሳቢ ችግር ሆኖ ብቅ ማለቱን ጠቅሷል፡፡ በተለይ ከመሬት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸው አገልግሎቶችን ወስኖ ከመስራት ይልቅ በአይመለከተኝም መንፈስ ወደላይኛው አካል የማንከባለልና አገልግሎት አሰጣጡን በማንዛዛት ህብረተሰቡንና መንግስትን የማራራቅ ዝንባሌዎች ጎልተው መታየታቸውን የከተማው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት መድረክ መገምገሙን የኢሳት የመስተዳድሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
“መሬት በሕገወጥ መንገድ ጭምር የራስ ለማድረግ የሚሞክሩ ግለሰቦችን ዝም ብለው የሚመለከቱ፣ለበላይ አካል ከማሳወቅ ውጪ በጉዳዩ እጃቸውን የማያስገቡ አመራሮች መኖራቸው እና ሕገወጥነት የመስፋፋት ምልክቶች መየታቸውን አገልግሎት ፈላጊው ህብረተሰብን ለእንግልትና ምሬት እንዲዳረግ አድርጎታል ተብሎአል።
ከላይ አስከታችኛው እርከን ባሉ የከተማዋ አስተዳደር አመራሮች መካከል ተናብቦ፣ተደጋግፎ የመስራት ሁኔታ አለመኖሩ፣ በርካታ ጉዳዮች በወቅቱ እንዳይፈቱ እንቅፋት እየሆነ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን ይህን ችግር በቀጣይ ሩብ ዓመት እንዲፈታ ከንቲባ ድሪባ መመሪያ መስጠታቸው ታውቆአል፡፡
በአስተዳደሩ በተለይ በከፍተኛ አመራር ላይ የሚገኙ ሹመኞች በወሰንነው ጉዳይ በሙስና ልንጠየቅ እንችላለን በሚል ከኃላፊነት የመሸሽ አዝማሚዎችን ማሳየታቸው የግምገማው ዋንኛ ትኩረት ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መስተዳድሩ በቦሌ ክፍለከተማ ቤቶችን ማፍረስ ጀምሯል። የመስተዳድሩን እርምጃ የተቃወሙ ከ20 ያላነሱ ሰዎች መታሰራቸውም ታውቋል። ኢሳት በዚሁ ክፍለከተማ የ900 አባወራ ቤቶች እንደሚፈርሱ መግለጹ ይታወቃል።
በአዳማ ከተማም በተመሳሳይ መንገድ በጨፌ አባ ገዳ አዳራሽ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቤቶቻቸውን እንዲያፈርሱ ትእዛዝ ታላልፎባቸዋል። ህዝቡ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት ነዋሪዎች፣ ለማፍረስ ፈቃደኛ ያልሆኑት 7 አመት እንደሚታሰሩና 50 ሺ ብር ድረስ እንደሚከፍሉ ተነግሯቸዋል። በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት 4 ወራት ዉሀ መቋረጡንም ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።